ቀጥታ፡

የባህር በር ለቀጣናዊ ሰላም፤ ለአህጉራዊ ብልፅግና !

(በፋኑኤል ዳዊት፤ ከሀዋሳ ኢዜአ ቅርንጫፍ)

ሀዋሳ፤ የካቲት 17/2018 (ኢዜአ):-  የባህር በር ለቀጣናዊ ሰላም፤ ለአህጉራዊ ብልፅግና !

የባህር በር የአንድ ሀገር መሬት በቀጥታ ከውቅያኖስ ወይም ከባህር ጋር የሚገናኝበት ዳርቻ ሲሆን አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ግንኙቶች የሚከናወኑበት መተላለፊያም ነው። 

የባህር በር ከንግድና ከሌሎች የኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ባሻገር የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነትና ትስስር የቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ ጸጥታንና አስተማማኝ ደህንነት ለማስጠበቅ ጉልህ እንደሆነ ይገለጻል። 

ስለዚህም ነው የባህር በር የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰደውና የባህር በር አልባ ሀገር መሆን እንደ ከባድ ችግር የሚታየው። 

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከሚጋፈጧቸው በርካታ ችግሮች መካከል የሸቀጦች የምልልስ ጊዜ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በአለም አቀፍ ንግድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራል። 

በዚህም ሳቢያ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በትራንስፖርትና በማሪታይም ንግድ በጎረቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ ይሆናሉ። ይህም ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ ስለሚያስገድድ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጽዕኖው ይጎላል። 

ጥገኝነቱ ለጂኦፖለቲካዊ ውጥረት እና አለመረጋጋት የማጋለጥ እድሉ የሰፋ ነው። በአንዱ ሀገር የሚነሳው የፖለቲካ ትኩሳት ወይም የፖለቲካ አለመረጋጋት በተለይም የባህር በር የሌለውን ሀገር ሳይወድ በግድ ሰለባ የማድረግ ወይም ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው። 

ከባህር በር ተነጥላ የማታውቀው ኢትዮጵያ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ለዘመናት የባህር በር አልባ ሀገር የመሆን ክስተት በማስተናገዷ ከላይ በጥቂቱ የጠቀስናቸውን ችግሮች ስትጋፈጠው ቆይታ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ሁሌም ህዝቡን ሲቆጨውና ሲያንገበግበው የቆየ ጉዳይ ሲሆን በጥቂት ግለሰቦች ይሁንታ የተቸረ ሀገርን ዝግ አድርጎ የማቆየት ሴራ ነው። ይህ ሁኔታ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየውን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ገሃድ ያወጣ  የትውልዱ ጥያቄ እንዲሆን አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ይፋ በማድረግ ትውልዱ በውስጡ ይዞት የኖረውን ቁጭት ግልጽ እንዲወጣ አድርገዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ 65ኛ ዓመቱን ባከበረው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከታች ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምፅዋ ጫፍ የሚያጋጥሙ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚችልና ለቀጣናዊ ሰላም የሚሰራ ተቋም እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አክለው እንደገለፁት ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም ብሎም ለአፍሪካ ብልፅግና የሚሰራ ተቋም እየገነባች መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ጠቀሜታው ለገረቤት ሃገራትና ለሌሎችም መሆኑን በግልፅ አስቀምጠዋል።  

በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን እንደገለፁትም፤ ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ተነጥላ ከማታውቀው የባህር በር ባለቤትነት በታሪክ ላለፉት 30 ዓመታት ተገልላ መቆየቷ ለጂኦ ፖለቲካዊና ጂኦ ኢኮኖሚክስ ችግሮች አጋልጧታል፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የዲፕሎማሲ አሰልጣኝና የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ (ዶ/ር) በመንግስትነትና ከባህር በር ሳትነጠል ለዘመናት የኖረች ሀገር በሴራ ፖለቲካ ዝግ ሀገር እንድትሆን መደረጉ የታሪክ ስህተት መሆኑን አንስተዋል። 

የዓለም ሀገራት በተለያየ ምክንያት ከባህር በር እንዳይገለሉ የሚያስቀምጡት ህጎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት ከዓለም ጋር በቀጥታ እንዳትገናኝ፣ የባህር በር አልባ ሀገር እንድትሆን መደረጉ ተቀባይነት የሌለውና በትውልዱ ዘንድ ምላሽ አጥቶ የተቀመጠ ጥያቄ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደመቀ አጭሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጥያቄው የትውልድ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ በሴራና አግባብ ባልሆነ መንገድ የባህር በር ባለቤትነትን እንዳጣች ነው የሚናገሩት፡፡

ያለፈው ስርዓት የባህር በር ጉዳይን በግልም ይሁን በቡድን እንዲነሳ ባለመፈለጉ ውስጥ ውስጡን የቆየውን ይህ ጉዳይ አሁን ላይ መንግስት ኃላፊነትን ወስዶ እስከ መቼ ተዘግተን እንኖራለን ብሎ በይፋ ማንሳቱ ወሳኝና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ምሁሩ አንሰተዋል። 

ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቅማ የውጭ ግንኙነቶችን፣ ንግድና እንዲሁም በዚህም በቀጠናው ተፅዕኖ የመፍጠር ሀይል እንደነበራት አውስተው ከባህር በር በተለይም ከቀይ ባህር ተነጥላ አትታይም ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ንጉስ በላይ (ዶ/ር) ናቸው። 

ይሁን እንጂ ከአውሮፓ ቅኝ ገዢ ሀገራት መካከል ኢጣሊያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1890 ዎቹ ጀምሮ እስከ 1950 ዎቹ ኤርትራን በመግዛቷ ከባህር በር ለመገለል አደጋ የዳረጋት ክስተት አጋጥሟት እንደነበር እና ይህም በታሪኳ ዝግ ሀገር እንድትሆን ማድረጉን አስታውሰዋል። 

ይሁን እንጂ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1952 ጀምሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን በመዋሃዷ የባህር በር ባለቤትነት መብት ድጋሚ እንድታገኝ በማድረግ እስከ 1991 ድረስ ተጠቃሚ እንደነበረች አንስተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የእንግሊዘኛ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር) በታሪኳ ከቀይ ባህር ተነጥላ የማታውቀው ሀገር ኢትዮጵያ የኤርትራን የሀገርነት ጥያቄ ለመመለስ ሲባል የባህር በርን ሙሉ በሙሉ እንድታጣ መደረጉ ፈጽሞ ተገቢነት የሌለውና ፈጣን ምላሽ የሚሻ የትውልዱ የቁጭት ጥያቄ ነው ብለዋል። 

በተለይም ኢህአደግ ኢትዮጵያን በመራባቸው ዓመታት ይህ ጉዳይ እንደ ጥያቄ ማንሳት እንደወንጀል የሚታይ ሆኖ መዝለቁ ስርዓቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ ታሪክንና የሀገሪቷን የመጻኢ ዕጣ ፈንታ ያልተመለከተ መሆኑ ጥያቄ ሲያስነሳበት እንደነበር አስታውሰዋል። 

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለወደብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በቀጥታ የተሳሰረ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚገልፁት አምባሳደር ማርቆስ (ዶ/ር)  በተፈጠረ የፖለቲካ ስህተት ከባህር ተዘግታ መቆየቷ አግባብ ስላልሆነ ጉዳዩ ፈጣን ምላሽን ይሻል ብለዋል።

ለዚህም በፖለቲካ ስህተትና በሴራ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዲመለስላት የዓለም ማህበረሰብ ጉዳዩን በግልጽ እንዲያውቀው ለማድረግ በተሰራ ስራ በጎ ምላሽ እየተገኘበት ነው ብለዋል።

ተገቢ ባልሆነ መንገድ የታጣውን የባህር በር ማግኘት የትውልዱ የዘመናት የቁጭት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ  መንግስት በቁርጠኝነት የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት አድንቀዋል።

ጥያቄው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለሚበራከቱበት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ሀገራቱ ላላቸው ተያይዝ የመበልፀግ ራዕይ መሳካት ወሳኝ ድርሻ ስላለው የጎረቤት ሀገራት ለጥያቄው በጎ ምላሽ ይሰጣሉ ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።  

የባህር በር ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ ለወታደራዊ ሀይል ፣ ለማናቸውም የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ መሳለጥ ተኪ የለሌለው እንደሆነ ያነሱት  ደመቀ(ዶ/ር)  ለኢትዮጵያ የመኖር እና ያለመኖር የህልውና ጥያቄ እንዲሁም የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ እንደሆነ አንስተው የተለያዩ ስልቶች በመከተል ዕድሎችን ለመጠቀም የተጀመረውን ጥረትን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ምሁሩ አክለውም በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ የጎረቤት ሀገራትም በጉዳዩ ዙሪያ በጎ ምላሽ በመስጠት ሊተባበሩ እንደሚገባ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ለቀጣናው ብሎም ለአህጉሩ የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት ለጥያቄው ድጋፋቸውን ሊሰጡ ይገባል ብለዋል። 

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት ያላቸውን ጥያቄ በፍትሃዊነትና በአግባቡ እየመለሱ ተያይዞ የመበልፀግ ዕድልን ለመጠቀም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ መመለስ ለሁሉም ጠቃሚ መሆኑን ሊረዱትና ሊቀበሉት ይገባል ያሉት ደግሞ ንጉስ (ዶ/ር) ናቸው።  

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተሳሰረና መነጣጠል የማይቻል እንደሆነ የሚገልፁት ምሁሩ ይህም ያላቸውን ዕምቅ አቅም አቀናጅተው እንዲጠቀሙና ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ የማድረግ ዕድልን የሚያሰፋ፤ ቀጣናውንም  የተረጋጋ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል ። 

የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለማንም የምንተወው አይደለም ትውልዱ እንዲመለስ የሚፈልገው ጥያቄ ነው ያሉት እንዳልካቸው (ዶ/ር) መንግስት በይፋ መጠየቁን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማሲ የተጀመሩ ጥረቶች እያስገኟቸው ያሉ በጎ ምላሾችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ምሁሩ አክለውም ያለውን አለም አቀፍ በጎ ምላሽ ከግምት በማስገባትም የአፍሪካ ቀንድም ሆኑ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ለጉዳዩ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ቀጣናዊ ብሎም በዚህ ውስጥ አህጉራዊ ብልፅግናን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም