የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትስስርን ከማሳለጥ ባለፈ ለአጀንዳ 2063 መሳካት መሰረት የሚጥሉ ናቸው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትስስርን ከማሳለጥ ባለፈ ለአጀንዳ 2063 መሳካት መሰረት የሚጥሉ ናቸው-ምሁራን
ደሴ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፡-- የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትስስርን ከማሳለጥ ባለፈ ለአጀንዳ 2063 መሳካት መሰረት የሚጥሉ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ ከዓድዋ ድል እስከ አጀንዳ 2063 ስኬት ለአፍሪካ ነጻነትና ብልጽግና ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኢትዮጵያ ትናንት ለአፍሪካውያን ነጻነት ፋና ወጊ ሆና እንደዘለቀች ሁሉ፣ ዛሬም የአህጉሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ትስስር በመምራት ላይ መሆኗን አመልክተዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ካሴ እንደሚሉት፣ የአድዋ ድል የፖለቲካ ነጻነት መሰረት እንደነበረው ሁሉ፣ አሁን በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ነጻነት ምሶሶዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለሀገራዊ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የጋራ ዕድገት ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተሰሩ ሥራዎች አለም ያደነቀው ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ምስራቅ አፍሪካን በሃይል በማስተሳሰር በጋራ የመበልጸግ ራዕይን የሚያሳካ ነው ብለዋል።
ሀገሪቷ በዲጂታላይዜሽን እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት፣ በኢንቨስትመንትና በኢንዱስትሪ መስክ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራችና የፓን አፍሪካኒዝም ተሟጋች እንደመሆኗ፣ "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት" የሚለውን መርህ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች ብለዋል።
ይህም የአህጉሪቱን ነጻነት ለማረጋገጥና የአፍሪካን መፃኢ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ካላት ቁርጠኝነት የመነጨ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል መምህር እንድሪስ ሁሴን በበኩላቸው፣ኢትዮጵያ የህብረቱ ዋና መቀመጫ እንደመሆኗ የአፍሪካን የ2063 አጀንዳ ስኬታማ እንዲሆን ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀሪው አለም ጋር ለማስተሳሰር እያደረገ ያለው ጥረት አህጉራዊ ብሎም አለም አቀፋዊ ትስስር የመፍጠሩን ግብ የሚደግፍ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ተጀምሮ አሁን ላይ በሁሉም አካባቢዎች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት ለአፍሪካ ከተሞች የዘመናዊነት ተምሳሌት መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችን የነጻነት ተስፋ እንዳበራች ሁሉ፣ አሁንም በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ትገኛለች ብለዋል።
የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ትላልቅ አለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ የአፍሪካ ኩራትና ተመራጭ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት በጥናትና ምርምር በመደገፍ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።