ቀጥታ፡

የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነፃነት ትግል ያሳረፈችውን ደማቅ አሻራ የሚያንጸባርቅ ነው

አዲስ አበባ፤የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነፃነት ትግል ያሳረፈችውን ደማቅ አሻራ የሚያንጸባርቅ መሆኑን በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴል ሎሲ ገለጹ።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በሰለጠኑበት ኮልፌ ፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የተሰየመው የመታሰቢያ ሙዚየም ተመርቋል።

በምርቃ መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴል ሎሲ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የነፃነት ትግል የጎላ አስተዋፅኦ አበርክታለች።

ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን የተላበሱ መሆናቸውን ገልጸው፤ የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አባት የሆኑትን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ማሰልጠናቸውን አወድሰዋል።

ኔልሰን ማንዴላ ለስልጠና ሲመጡ ማንነታቸውን ቀይረው እንደነበር አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ትግል ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ያሳያል ብለዋል።

የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም የሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካውያን የትብብርና አንድነት መገለጫ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት አለባቸው የሚለውን በተግባር ያሳየች መሆኑንም ገልጸዋል።

የዓለም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነው የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያንን ጀግንነትና አይበገሬነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም የሁለቱ ሀገራት ወጣቶች ጀግንነትና ትብብርን ለትውልድ የሚያስተላልፉበት ሁነት መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ሁለት ሀገሮች ነገር ግን በታሪክ እና በጀግንነት አንድ ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቱሪዝም ዘርፍ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቅሰው፤ትብብራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ለመሰልጠን የመረጡት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና የዓለም ጥቁር ህዝቦች ምልክት በመሆኗ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም