የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት ጥሩ መሰረት እያኖረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት ጥሩ መሰረት እያኖረ ነው
ወልቂጤ ፤ የካቲት17/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን የወልቂጤ እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በቀጣዮቹ አምስት አመታት የሚተገበር እቅድ ተነድፎ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ የሚተገበረው የ2030 ስትራቴጂ ባለፉት አምስት ዓመታት ጠንካራ መሰረት የያዘውን የዲጅታል ዘርፍ በማስቀጠል ኢትዮጵያን የዲጂታል ኢንቨስትመንት ማዕከል የማድረግ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛል።
በእቅዱ መሰረትም ዜጎች ሁሉ በዲጂታል ክህሎት የሰለጠኑ እንዲሆኑ የማድረግ ብሎም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ዲጂታል ቴክኖሎጂን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ይሆናል።
የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ለእቅዱ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ በዚሁ ልክ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልቂጤ እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያ የዲጅታል ልማት ስትራቴጂ በተለይም ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ቸርነት ዘርጋ፤ በዲጅታል ልማት ትግበራና ስትራቴጂ ኢትዮጵያ የሚታይ ለውጥና የሚጨበጥ ውጤት ማምጣቷን ተናግረዋል።
የዘርፉ ልማት በተለይም ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እንዲሁም ለምርምር ስራዎች ውጤታማነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
በዚህ ረገድ በተለየም የዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የመንግስትን ጥረት በምርምር ጭምር በመደገፍና በማገዝ ለዲጅታል 2030 መሳካት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳይሬክተር አበበ ሎላሞ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የዲጅታል አገልግሎት ከትምህርት ተደራሽነት፣ ጥራትና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን በመላው ዓለም በቀላሉ ለማስተዋወቅ መልካም እድል ስለመሆኑ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በ"ዲጂታል 2025" ስትራቴጂ ባከናወነቻቸው ተግባራት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ምሁራኑ መንግስት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ለዲጂታል መሰረተ ልማት የሰጠው ትኩረት ለቀጣዩ "ዲጂታል 2030" እቅድ መሳካት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን አስረድተዋል።