ቀጥታ፡

የኔልሰን ማንዴላ የመታሰቢያ ሙዚየም ተመረቀ

አዲስ አበባ፤የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በሰለጠኑበት ኮልፌ ፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የተሰየመው የመታሰቢያ ሙዚየም ተመርቋል።

በምረቃ መርሃግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖሊስ ምስረታ 117 ዓመታትን ያስቆጠረ ከአፍሪካ ቀዳሚው ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ለአፍሪካ የነፃነት ትግል የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸው፤ የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አባት የሆኑትን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ አሰልጥኗል ብለዋል።

ኔልሰን ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ ትግልን ለመቀላቀል እኤአ በ1962 በኢትዮጵያ ለወራት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ለመሰልጠን የመረጡት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና የዓለም ጥቁር ህዝቦች ምልክት በመሆኗ ነው ብለዋል።

ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያውያን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች መሰልጠናቸውን ጠቅሰው፤ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔ፣ አስር አለቃ ፈቃዱ ወንድሞ ከአሰልጣኞች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖሊስ እውቀትና ልምዱን በማካፈል ለደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።

የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላት ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም