ቀጥታ፡

በሁሉም ክልሎች የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦በሁሉም ክልሎች የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮጵያ የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የኢንዱስትሪ ሽግግር በማፋጠን ላይ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።

የይርጋለም፣ ቡሬና ቡልቡላ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በእንስሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባትና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር ጉልህ ጠቀሜታ እያበረከቱ ነው።

የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹም የአርሶ አደሩን የገበያ ትስስር በማሳለጥ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ውጭ ምንዛሬና በዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል።

ይህም የኢትዮጵያን የግብርና ጥሬ ምርት ዕሴት ወደታከለባቸው የፋብሪካ ምርት ውጤቶች በማሸጋገር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ወሳኝ አቅምን በመፍጠር ላይ ናቸው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉትም፤ የግብርና ምርታማነትን በማዘመን የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል ስኬት እየተመዘገበ ነው።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት የተመዘገበው እመርታዊ ስኬትም ለአግሮ-ፕሮሰሲንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የመደመር መንግስት ዕይታ ለዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በሰጡት ስልጠናም የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ የማስፋት ስራ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን በሁሉም ክልሎች በመገንባት የግብርና ኢንዱስትሪ ሽግግርን ማቀላጠፍ እንደሚገባ አጽንኦት እንደተሰጠው አንስተዋል።

በዚህም በሁሉም ክልሎች የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪዎችን ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል የመሬትና የቅድመ ዝግጅ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሎችን የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ግንባታ ውጤታማ ለማድረግም አስፈላጊውን የማስተባበር፣ የመምራትና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሦስት የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ኢንዱስትሪ ሽግግርን ማፋጠን በሚያስችል የምርታማነት አቅም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ዕሴት የታከለበት የግብርና ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለአብነትም 39 የሚደርሱ የምግብ ዘይት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሟቸው የቅባት እህል የሰብል ምርቶችም የአርሶ አደሮች ምርትማነት በማሻሻል ወጪ ንግድ ላይ አይነተኛ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የግብርና ምርታማነትና የኢንዱስትሪ ተመጋጋቢነት አቅም በማሳደግ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፈጣን መዋቅራዊ ሽግግር መሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም