በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኘነው እውቀት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጥሮልናል- ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኘነው እውቀት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጥሮልናል- ሰልጣኞች
ሆሳዕና ፤ የካቲት 17/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኘነው እዉቀት ተጨማሪ ገቢ ለማግኝት አስችሎናል ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጠናውን የወሰዱ ዜጎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም በርካታ ወጣቶች አቅማቸውን ለማሳደግ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን ስልጠናውን በኦን ላይን እየተከታተሉ ናቸው።
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወሰዱ የመንግስት ሰራተኞች ያገኙት እውቀት ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉበትን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን ተጠቃሚ እያደረገን ነው ይላሉ፡፡
በየም ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ቸርነት ሰውነት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በመውሰድ ባገኙት እውቀት ተጨማሪ ገቢ ለመፍጠር መቻላቸውን ይገልፃሉ።
በዚህም ከመደበኛ የመንግሥት ስራቸው ጎን ለጎን ሶፍትዌሮችን ከማበልፀግ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን በኦን ላይ በመስራት ከ365 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት ስለመቻላቸውም ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ አቶ ምስጋና ከበደ በበኩላቸው በስልጠናው ድረ ገፆችንና የሞባይል መተግበሪያዎችን በማልማት፤ መረጃዎችን የማደራጀት፤ የመተንተንና የተለያዩ ማሽኖችን በመጠቀም የተለያዩ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል በቂ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርት ፀጋነሽ ሞገስ እና የሶፍትዌር ኢንጂነሪነግ መምሕር የሆኑት አቶ መሳይ አስቻለው፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበራቸውን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ አለማቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በዚህም በዘርፉ የሚያሰለጥኗቸውን ተማሪዎች ለዓለም አቀፍ ገበያው በሚመጥን መልኩ ብቁ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል፡፡
ስልጠናው የተለያዩ መተግበሪያዎችን አልምተው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምህዳር እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን እየተከታተሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም ከ157 ሺህ በላይ ዜጎች የእውቅና ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡