ማንችስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/ 2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ቤንጃሚን ሼሽኮ በ71ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
በጨዋታው ላይ ኤቨርተን የተሻሉ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው ማንችስተር ዩናይትድ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብ በመቀየር አሸናፊ ሆኗል።
የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ሴን ላመንስ የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
በሊጉ 13ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ48 ነጥብ ደረጃውን ከአምስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
እንግሊዛዊው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በሊጉ አምስተኛ ድሉን አሳክቷል። ቡድኑ በካሪክ ስር እስከ አሁን አልተሸነፈም።
በአንጻሩ በሊጉ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኤቨርተን በ37 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።