ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ንጋት ከድምጽ አሰሚነት ወደ ተሰሚነት!
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መዝገብ ሲገለጥ የሚነበበው በክብር የቆመ የታሪክ መሠረት፣ ነገር ግን እንደ ጥንታዊነቷ ድምጿ ጎልቶ የማይሰማበት የቆየ አሠራር ነበር።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተመዘገበው ድል ግን ይሄንን የተገደበ ተሳትፎ በመስበር፣ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረክ ዋነኛ ተዋናይ ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
የለውጡ መንግሥት ዲፕሎማሲን እንደ ሀገራዊ ሉዓላዊነት መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብልጽግና ምንጭ በመቁጠር በብርቱ ሠርቷል። ዛሬ የዚህ ብልህ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ፍሬ እያፈራ፣ የሰላም እና የትብብር ጥረቱ አዝመራ እየታጨደ ነው፡፡
ለዚህ ሥር ነቀል ለውጥና ኢትዮጵያን በጎረቤት ሀገራት እና በአህጉር ደረጃ ያላትን አቀራራቢ ሚና በማጠናከር፣ የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የነበረውን የቆየ እሳቤ መቀየር ተችሏል።
ሀገርን ማዕከል ያደረገ፣ ክብሯን እና ጥቅሟን የሚያስከብር ተለዋዋጭ ዲፕሎማሲ በመከተል ለተገኘው ስኬት ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቁልፍ መሐንዲስ ናቸው።
የኢትዮጵያ ወደ BRICS+ መቀላቀል፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት መድረኮች ላይ የሚቀነቀነው አቋሟ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መሪዎች ዘንድ ያገኘችው ከፍ ያለ ተቀባይነት የዚሁ የጠራ ራዕይ ውጤቶች ናቸው።
ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው፡፡