የፓስፖርት አገልግሎት በቅርብ ተደራሽ መደረጉ የዜጎችን እንግልት አስቀርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የፓስፖርት አገልግሎት በቅርብ ተደራሽ መደረጉ የዜጎችን እንግልት አስቀርቷል
ጎንደር፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፡- የፓስፖርት አገልግሎትን በአቅራቢያቸው ማግኘታቸው ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና ወጪ የሚያስቀር መሆኑን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በጎንደር ከተማ በከፈተው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የፓስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪ ሶፍያ መሀመድ፣ ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለማግኘት ወደ ሌሎች ከተሞች በመሄድ ለከፍተኛ ወጪና ድካም ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
አገልግሎቱ በቅርበት መጀመሩ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይደርስ የነበረውን አላስፈላጊ ወጪና እንግልት ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ ኤፍሬም ገበየሁ በበኩሉ፣ ፓስፖርት ለማውጣትና ለማደስ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ ግዴታ ስለነበር በተገልጋዩ ዘንድ ከፍተኛ ምሬት እንደነበር ገልጿል።
አገልግሎቱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ፓስፖርት መስጠት መጀመሩ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በጎንደር ቅርንጫፍ መክፈቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ህዝቡ ሲያነሳ የቆየውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል፡፡
የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አስቻለው እዘዘው እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል በአምስት ከተሞች ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
የጎንደር ቅርንጫፍም አገልግሎቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጅታል አሰራር መጀመሩን ጠቁመው፣ 400 ለሚደርሱ አገልግሎት ፈላጊዎችም በአንድ ቀን ብቻ ፓስፖርት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በአገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ-ስርአቱ ላይ የከተማው ከፍተኛ አመራሮችንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡