ቀጥታ፡

በመዲናዋ የ97 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ለመገንባት ከታቀደው 100 ሺህ ቤቶች ውስጥ የ97 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከተማ አስተዳደሩ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ ልማት ውስጥ ለቤት ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል።

 


 

በ2018 ዓ.ም ለማከናወን ከታቀደው 100 ሺህ የቤቶች ግንባታ ዉስጥ የ97 ሺህ ቤቶች ግንባታ በአስደናቂ ሁኔታ እየተፋጠነ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ ካሉ 17 ሳይቶች መካከል በገርጂ፣ በቱሉ ዲምቱ፣ በገላን ጉራ (የመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፍ)፣ በአቃቂ ቃሊቲ (ወርቁ ሰፈር) እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ የገበያ ማዕከል እየተገነቡ ያሉትን ቤቶች አፈጻጸም ዛሬ መገምገሙን ጠቁመዋል።

ግምግማ የተደረገባቸው ሳይቶች ፕሮጀክቶች ከተጀመሩ ከ6 እስከ 7 ወር ቢሆንም፣ ቀን እና ማታ ያለማቋረጥ በመስራት ፤ እጅግ ትጉ በሆኑ ኢትዮጵያዊ ኮንትራክተሮች፣ ማህበራት፣ አማካሪዎች፣ ትጉ አመራሮች እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአሁኑ ወቅት አበረታች ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በሳይቶቹ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና በርካታ ኮንትራክተሮችና ማህበራት በአዲስ የሥራ ተነሳሽነትና በትጋት እየተሰሩ ይገኛል ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት የቤቶቹ ግንባታ ፍጥነት ብቻ ላይ ሳይሆን፣ ከቤት አቅርቦት የዘለለ በተሻሻለ ዲዛይን ጤናማ፣ ውብና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን መገንባት ላይ ነው ብለዋል።


 

የግንባታ ጥራት ለማረጋገጥ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአማካሪነት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እየተገነቡ ካሉት ቤቶች ውስጥ 50 ሺዎቹ በከተማው በጀት የሚገነቡ ሲሆን የተቀሩት 50 ሺዎቹ ደግሞ የሚገነቡት በመንግስትና የግል አጋርነት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከለውጡ በፊት እንደዚህ አይነት ሰፊ የቤት ልማት አይደለም በከተማው በጀትና በአንድ አመት ቀርቶ በተለመደው የባንክ ብድር እንኳን በየአምስት አመቱ 100 ሺህ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በሚሊዮኖች ተመዝግበው ለረጅም አመታት እስከ ዛሬ የሚጠባበቁ እና ከ60 ቢሊዮን በላይ የኮንዶሚንዬም የቦንድ እዳን ተረክበን ለመክፈል እና ለማስተናገድ ባልተገደደን ነበር ብለዋል።

አሁን እየተገነባ ያለው ቤት ከነዋሪዎች ሰፊ ፍላጎት አንጻር አቅርቦቱ ገና ቢሆንም፣ የቤት ችግርን በዘላቂነት የመፍታት ስራችን ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ላይ ያሰፈሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም