ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርት ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት ምቹ ዕድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርት ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ምቹ የአሰራርና የድጋፍ አሰጣጥ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከተማ አቀፍ የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ የፓናል ውይይት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና የኢንዱስትሪ ተዋንያን በተገኙበት በተካሄደው ፓናል ላይ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የምትሰጠው ትኩረት አስደናቂ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ብሔራዊ ንቅናቄም ለዘርፉ ማነቆዎች መፍትሔ በመስጠት የምርታማነትን የሚያሳደግ እመርታዊ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የአምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረውን ድርሻ የሚያጎለብት የቦታና የፋይናንስ አቅርቦት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ መኮንን ያኢ በተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅምን ማሳደግ የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር አምራች ኢንዱስትሪዎች በመሬት አቅርቦት ላይ የሚነሷቸውን ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታሰው ፋንታው፤ የኢንዱስትሪ ዕድገትን ለማስቀጠል የፋይናንስና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በጉሙሩክ ኮሚሽን የጉሙሩክ አሰራር ልማት ዳይሬክተር እንዳሻው ተመስገን በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በርካታ የሕግና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረጉ የአሰራር ማሻሻያዎች የድጋፍ ማዕቀፎችን በሚገባ በመጠቀም ምርታማነትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ደበበ (ዶ/ር)፤ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን የሚያግዝ መፍትሔ አመላካች የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት መፍትሔ አመላካች የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ገንቢ ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የውይይት መድረኩን ያጠቃለሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፤ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በዚህም በማሽነሪ ሊዝ፣ በፋይናንስና በማስፋፊያ መሬት አቅርቦት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የምርት ተወዳዳሪነትና ብቃት የሚያሻሽል ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችም በሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል የምርትን ጥራትና በብዛት የማምረት አቅምን መገንባት እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም