ቀጥታ፡

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት መሠረትና የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው -ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ

ባህርዳር ፣የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፡ - ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት መሠረትና የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን በመከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ገለጹ።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ እዝ እና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አባላት 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ከተማ  በውይይት አክብረዋል።


 

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ፣ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት መሰረትና የመላው ጥቁር ህዝቦች የድል አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል የአሸናፊነት ምሥጢር፤ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት በጋራ መቆማቸው ነው ብለዋል።

ይህ የጀግንነት ታሪክ ከሀገር አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የድል ብስራትና የታሪክ እጥፋት ያመጣ መሆኑንም አብራርተዋል። 

በዚህ ታላቅ ገድል የተረከብናትን ታላቅ ሀገር ክብሯንና ሉአላዊነቷን በጀግንነት ጠብቀን ማስቀጠል ችለናል፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ የባዕዳንን ተልእኮ የተቀበሉ ባንዳዎችንና የጥፋት ተግባራቸውን ለመፈፀም የሚጥሩ ጽንፈኞችን ተከታትሎ ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የትኛውንም ጥቃቶች መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም