ቀጥታ፡

የሴቶች አደረጃጀቶች በጠቅላላ ምርጫው የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር እየሰሩ ነው

መቱ፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፡- ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር አበክረው እየሰሩ  መሆናቸውን በኢሉባቦር ዞን የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶች ገለጹ።

የኢሉባቦር ዞን ሴቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሀገሬ ሀብታሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፌዴሬሽኑ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎንና ሚና ለማጉላት እየሰራ ነው።

በዚህም የዞኑ ሴቶች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድሕረ-ምርጫ ሂደቶች በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ የምርጫ ሥነ-ምግባር ትምህርቶችን በየደረጃው ለሚገኙ ሴቶች በመስጠት ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገርን የመገንባት፤ መንግስትንም የመመስረት ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ በሆነው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ትልቅ ቦታ አለው ያሉት ወይዘሮ ሀገሬ፣ የዞኑ ሴቶች ለምርጫው ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የዞኑ ሴቶች ማሕበር ሊቀመንበር ወይዘሮ አባይነሽ ሙሉነህ በበኩላቸው፣ የዞኑ ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማህበሩ በየደረጃው ግንዛቤ የማስፋት ስራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የሴቶችን አደረጃጀቶች በማጠናከር በምርጫው ሂደቶች ውስጥ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ዋነኛ ተልዕኮችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሴቶች በምርጫው በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት  የግንዛቤ ማሳደጊያ መድረኮችን በማዘጋጀት ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህዝቡን የልማት ፍላጎትን ይበልጥ ለማሟላትና ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከማጠናከር ረገድ አደረጃጀቶቹ ለምርጫው ስኬታማነት የጀመሯቸውን ተግባራት አጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

በተለይ ሴቶች ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ውስጥ ካላቸው ቁጥር ልክ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ እንዲቻል ጠቅላላ ምርጫው ወሳኝነት እንዳለው የዞኑ የሴቶች አደረጃጀት አመራሮቹ  አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም