የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች፣ በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚኖረውን የእርጥበት አየር ሁኔታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች፣ በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚኖረውን የእርጥበት አየር ሁኔታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች፣ በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚኖረውን የእርጥበት አየር ሁኔታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ኢንስቲትዩቱ ከየካቲት 14 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ አንጻራዊ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልጿል።
በተለይም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ እና በመካከለኛው ዝቅተኛ አካባቢዎች የሚታየው እርጥበት፤ ለአፈር ዝግጅት፣ ለዘር ዝግጅትና ለዘር መዝራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።
የሚገኘው እርጥበት ለግጦሽ ሳር በቀል፣ ለቋሚ ተክሎች እድገትና ለሰውና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክቷል፡፡
በላይኛው አዋሽ፣ በላይኛውና በመካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ በኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆ እንዲሁም በጥቂቱ በላይኛው ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ መጠነኛ ዝናብ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በተጠቀሱት ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ የገፀ-ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖር ተመላክቷል።
በሌላ በኩል የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ላይ ደረቃማ ቀናት እንደሚስተናገዱ በመግለጫው ተጠቅሷል።