የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው
ደብረብርሃን፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ የተሰሩ ሥራዎች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳላቸው የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
''የወጣቶች መሪነት ለዘላቂ ሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ በወጣቶች ተጠቃሚነትና ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት በደብረ ብርሃን ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዘላለም አረጋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ በክልሉ የወጣቶችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የወጣቱን ጥያቄ እየመለሱ ነው ብለዋል።
ቢሮው የወጣቶችን ተሳታፊነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግም በሥነ-ምግባርና ሰብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ ሥራ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ወጣቶች ለሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ የተሰሩ ሥራዎች ለዘላቂ ሰላም የራሱን ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
በሥነ-ምግባር የታነጸ ወጣት በሀገሩ ጉዳይ ዘብ የሚቆም መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት በምታከናውነው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በንቃት መሳተፍና ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፣ በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋጋጥ በተደረገው ጥረት ወጣቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ሰላምን ለማጽናትና ልማቱን ለማስቀጠል ወጣቱ ከጸጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ራሄል ይመር ወጣቱ ለሰላም ዘብ ከመቆም ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።
ወጣት ኤፍሬም ጎጨ በበኩሉ መንግስት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አመልክቷል።
በዚህም ወጣቶች በተመቻቸላቸው የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም የብድር አቅርቦት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ መቻላቸውን አንስቷል።
የአካባቢን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጧል።