የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል ሲሉ የዘርፉ ተዋናዮች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 469 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷ የሚታወስ ሲሆን በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ ከሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት አቅዳ እየሰራች ትገኛለች፡፡
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በግብርናው ዘርፍ የቡና ምርታማነት ላይ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
በኦሮሚያ ክልል የቡና አልሚና ላኪ የሆኑት አቶ ፈጠነ የኋላሸት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በተለይ አረንጓዴ አሻራ ትልቅ አስተዋጾ ማበርከቱን ተናግረዋል
ባለፉት ዓመታትም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተከታታይነት መከናወኑ ቡናን ለማምረት ተስማሚ ሥርዓተ ምህዳርና የአየር ሁኔታ እንዲኖር ማስቻሉን ነው ያነሱት።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቡና መስክ ላይ የተሰማሩት አንዷለም ፋንታ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ የማህበሩ አባላት በስፋት በመሳተፍ ልማቱን እያገዝን እንገኛለን ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቡና ምርታማነታችንን ለማሳደግ የአካባቢውን የተፈጥሮ ገጽታ መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሲዳማ ክልል በቡና አቅራቢነት የተሰማሩት አባተ ኪሾ ናቸው ።
አስተያየት ሰጪዎቹ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን እና ዝርያዎችን ለተከላ ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዘሪሁን ቃሚሶ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ሀገራችን ከቡናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንደ ሀገር ማከናወን ከጀመርን በኋላ ከ8 ቢሊየን በላይ የቡና ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል።