ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ካሉ ተጨባጭ ውጤቶች የመነጨ ነው - የዘርፉ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ በመሬት ላይ ካሉ ተጨባጭ የልማት ሥራዎችና ስኬቶች የመነጨ መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ መግለጻቸው ይታወሳል። 

መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው እርምጃዎች የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ በማውረድ ትልቅ ስኬት መመዝገቡንም አመልክተዋል፡፡

በዚህም የዋጋ ንረትን ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ነጠላ አሃዝ በማውረድ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰው፥ አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል። 

የኢኮኖሚ ምሁሩ ደረጄ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለታየው ተከታታይ ዕድገት መሠረት ሆኗል። 

በተለይም በግብርና ዘርፍ ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በሆነው በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ "ኢትዮጵያ ታምርት" በተሰኘው ብሔራዊ ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አምራቾች አቅም እንዲጠናከርና የገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በማዕድን ልማት ዘርፉ ሌላው አስደናቂ ውጤት እየተመዘገበበት ያለ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን ጠቁመው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሀገሪቱን ዕድገት እያረጋገጡ መሆናቸው የዘንድሮው የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ትንበያ ስኬታማ እንደሚሆን ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የኢኮኖሚ ምሁር ጀማል መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ዕድገት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ይህ ዕድገት ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መስኮችን ለማስፋፋት እና ሌሎች ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚያግዝ አስታውቀዋል። 

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ውጤት እያመጡ መሆኑንና ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ማድረግ መቻሉ አስደናቂ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት የኤክስፖርት ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ መቻሉ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ምሁራኑ አስረድተዋል። 

ይህም በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

አሁን እየተወሰዱ ያሉ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት የላቀ የብልጽግና ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ምሁራኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም