ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት እና ሳዑዲ አረቢያ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ሳዑዲ አረቢያ በሰላም፣ ልማት እና ዲፕሎማሲ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሌድ ቢን አብዱልከሪም ኤል- ከሀርጂ(ኢ/ር) ከተመራ ልዑክ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አፍሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ለረጅም ጊዜ የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ትብብሩ በጥልቅ የባህል፣ የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውስተዋል።

ሳዑዲ አረቢያ በአፍሪካ ያላትን ዘላቂ ትብብር እና በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን ኢንቨስትመንት አልፎም በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ገንቢ ሚና አድንቀዋል።


 

ሳዑዲ አረቢያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመቀናጀት በሊቢያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች እያሳየች ያለውን የዲፕሎማሲ ድጋፍ እና ተሳትፎ አዎንታዊ መሆኑን አመልክተዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሌድ ቢን አብዱልከሪም ኤል- ከሀርጂ በበኩላቸው የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ በልማት፣ በሰላም እና በባለብዙ ወገን ትብብር ያለውን የመሪነት ሚና አንስተዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ልማት፣ ሰላም፣ ደህንነት እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ህብረትና ሳዑዲ አረቢያ ያላቸውን ግንኙነት በጋራ መከባበር መንፈስ፣ በወዳጅነት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ በመመስረት የበለጠ ለማጠናከር የጋራ ፍላጎት ማሳየታቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም