የብልፅግና ፓርቲ ዋነኛ ዓላማ ትናንትን በማከም ነገን የተሻለ ማድረግ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ ዋነኛ ዓላማ ትናንትን በማከም ነገን የተሻለ ማድረግ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)
ቦንጋ፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፡- የብልፅግና ፓርቲ ዋነኛ ዓላማ ትናንትን በማከም ነገን የተሻለ ማድረግ ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ምልክቱን(የስንዴ ነዶ) እና ማኒፌስቶ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት የብልፅግና ፓርቲ ዋነኛ አላማ በሀገረ መንግስቱ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያጋጠመውንና ትናንትን በማከም ነገን የተሻለ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ ያጋጠመውን የተዛባ መዋቅራዊ ችግር በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ለመፍታት ፓርቲው ባደረገው ጥረት ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በዚህም በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት በአለም እውቅና የተሰጠውን ድል ማስመዝገቡን ጠቅሰው የዘመናት ቁጭት የነበረውን የህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል።
በክልሉም የግብርና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ፣ የገቢ አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች በተደረጉ ሰፊ ርብርቦች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
በማህበራዊ ዘርፍም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ተወዳዳሪና ብቁ ትውልድን መፍጠርና ጤናማ ትውልድን ለማፍራት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር እንደሀገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ በክልሉ ያሉ አቅሞችን ለይቶ የማልማት ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፤ የብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉና ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተደረገው ርብርብ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የህዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን አንስተው በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያን ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ መንገዱ ብልፅግና ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።