ከተሞችን የብልጽግና ማሳያ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን የብልጽግና ማሳያ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ውጤት እያመጡ ነው
አዳማ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ ከተሞችን የብልጽግና ማሳያ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለፁ።
ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት አመት የስድስት ወራት የሴክተር ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የክልሎች የዘርፉ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።
ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በወቅቱ እንደገለፁት በለውጡ መንግስት ከተሞችን የብልጽግና ማሳያ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው።
የከተማ ነዋሪዎች ህይወት ከመለወጥ፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ፣ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ከማዘመንና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግሮች ከማቃለል አኳያ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
የከተሞችን መሰረተ ልማት በማስፋፋትና ዲጂታል አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ተስፋ ሰጪ ተግባራት መከናወናቸውንም አመልክተዋል።
በተለይ የኮሪደር ልማት በከተሞች መሰረተ ልማት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ገፅታቸውን በመቀየር በኩል ተጨባጭ ለውጦች የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማቱ የመደመር መንግስት እሳቤዎች ውጤት የታየበትና የከተሞች የገፅታ ለውጥ ያየንበት ነው ሲሉም አክለዋል።
በዚህም ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ አቅም ባህል እየሆነ የመጣበት መሆኑን ጠቁመው ልማቱ የህዝብና የመንግስት ትብብር የታየበት እንደሆነም አንስተዋል።
በከተሞች የተገልጋዩን ህብረተሰብ ዕርካታ ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ከተሞች ለኑሮና ለስራ ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ተስፋ ሰጪ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አረንጓዴ ልማቱም የከተሞችን ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻለም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
በቀሪው ሁለተኛው ግማሸ በጀት ዓመት ዲጂታል አገልግሎትን ማስፋፋት፣ በተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ የውበትና አረንጓዴ ልማት ስራዎችን ማጠናከር፣ የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎችን በበለጠ የመመለስ ተግባራት በትኩረት እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።