ቀጥታ፡

በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ትብብር ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የጎላ ሚና ተጫውቷል

ገንዳ ውኃ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ትብብር ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የጎላ ሚና መጫወቱን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ። 

በአካባቢው የተፈጠረው ሰላም  ለረጅም ጊዜ ተዘግተው የነበሩ የትራንስፖርት መስመሮች ዳግም አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ አስችሏል።

የመምሪያው ኃላፊ ደረሰ አዱኛ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በዞኑ የመጣው ሰላም የሕዝቡና የፀጥታ አካላት የነቃ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ውጤት ነው። 

አመራሩ ያለ ሕዝብ ድጋፍ ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣ በመገንዘብ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ መስራቱንና በዚህም በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማሕበረሰቡ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በተገኘው ሰላም ከገንዳ ውኃ-ጎንደርና ከገንዳውኃ-ቋራ የሚወስዱ መንገዶች ለተሽከርካሪ ክፍት በመሆናቸው የንግድና ማሕበራዊ እንቅስቃሴው እንዲቀላጠፍ ማድረጉንም አመልክተዋል።

ሕዝቡ የአካበቢውን ሰላም በንቃት እንዲጠብቅ አደረጃጀቶች እየተጠናከሩ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪው ካሳሁን ጌታነህ፤ መንግሥት ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። 

እየታየ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን አጠናከረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። 

ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ እህትነሽ ማለደ በበኩላቸው፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ከመንግሥትና ከፀጥታ አካላት ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም