ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን እንወጣለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ምርጫ ሀገርንና ህዝብን የሚመራ መንግስት መመስረት የሚያስችል ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ  እንዲሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 

ከምርጫው ዋና ዋና የዝግጅት መርኃ ግብሮች መካከል አንዱ የሆነው የዕጩዎች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይም የመራጮች ምዝገባ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚከናወን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) እና የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ(ነእፓ)በዘንድሮው ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ለኢዜአ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ አባል እና የምርጫ ማናጀር ኢዮብ መሳፍንት እንደተናገሩት፣ ፓርቲው መሰረታዊ የሚባሉ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።


 

በአሁኑ ወቅትም ዕጩዎቹን በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ለምርጫው የውድድር ዘመን የሚያገለግሉ ዝርዝር የማኒፌስቶ እና የፖሊሲ ሰነዶች ዝግጅት መጠናቀቁንም አስረድተዋል።

የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ በበኩላቸው፣ ጠንካራ ሀገር እና መንግሥት የሚመሰረተው በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ብቻ መሆኑን ፓርቲው ያምናል  ብለዋል።

በዚህም  ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እስከ ታችኛው መዋቅሩ ድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


 

ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የማስመዝገብ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የፓርቲውን ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ ስራ በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ፓርቲው የሀገሪቱን ነባራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያስገባ ፖሊሲ ማዘጋጀቱንም ጨምረው ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ የአካታችነት ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ምርጫ ሀገርንና ህዝብን የሚመራ መንግስት መመስረት የሚያስችል ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲዎቹና አባሎቻቸው የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳና አጠቃላይ ሂደቱ ላይ ሕግን ተከትለው በአርአያነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠቁመው የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች ተቋማትም ስራቸውን በገለልተኝነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም