ቀጥታ፡

የሳይንስ ሙዚየም ለኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ የሳይንስ ሙዚየም ለኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ኪሩቤል መንበሩ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር አባላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሳይንስ ሙዚየምንና በሳይንስ ሙዚየም የሚገኘውን የጠፈር ምርምር ማዕከል (ፕላኔታሪየም) ጎብኝተዋል።

በዚህም የከዋክብት ምልከታ፣ የጠፈር ሳይንስ ገለጻ እንዲሁም የጠፈር ምርምር ማዕከል የጠፈር ዘጋቢ ፊልም ተመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ኪሩቤል መንበሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የሳይንስ ሙዚየሞች በአንድ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ጉልህ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ።

ይህ የሳይንስ ሙዚየም ማህበረሰቡ ስለ ሳይንስ ያለው አረዳድና እውቀት እንዲያድግ ከማድረጉም በላይ ለዘርፉ ያለውን ቀረቤታ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተገነባው የሳይንስ ሙዚየም በውስጡ በያዛቸውና ሳይንስን በቀላሉ ማስረዳት በሚያስችሉ ኤግዚቢሽኖች አማካኝነት ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።


 

ሙዚየሙ በተለይም ታዳጊዎችና ወጣቶች ለሳይንስ ቅርብ እንዲሆኑ ከማድረጉ ባለፈ በትምህርት የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር አይተው እንዲረዱ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

ማህበሩ በአቅም ግንባታ፣ በመሰረተ ልማት እና ታዳጊዎች በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት እንዲያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማህበሩ ለሁሉም ክፍት መሆኑን በመጥቀስ፣ ፍላጎቱ ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች አባል በመሆን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር የውጭ ጉዳዮች አስተባባሪ ክብረት አጽብሀ በበኩሉ፣ የጉብኝቱ ዓላማ በስፔስ ሳይንስ የሚከናወኑ ስራዎችን ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

ሳይንስ ሙዚየሙ ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ መንገድ ከመጥረጉ ባለፈ፣ ተመራማሪዎች ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግሯል።


 

ጉብኝቱ ስለጠፈር እውቀት እና ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ደግሞ ተማሪ ፍትህ ግርማ እና ጽዮን ብርሀኑ ናቸው።

የሳይንስ ሙዚየሙ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም