የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሸገር ከተማ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሸገር ከተማ ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሸገር ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ 13 ጨዋታዎችን አድርጎ በ10ሩ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 34 ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ32 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ እና አነስተኛ ግብ ያስተናገደ ቡድን ነው።
ተጋጣሚው ሸገር ከተማ እስከአሁን ባከናወናቸው 13 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጊዜ ድል ሲቀናው በቀሪ አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በ13ቱ ጨዋታዎች ላይ 21 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክከር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች መካከል በስምንቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ13ቱ ጨዋታዎች 22 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ27 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ያሸነፋቸው ጨዋታዎች ብዛት አራት ናቸው። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 23 ጎሎችን አስተናግዷል።
አዳማ ከተማ በ15 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።