በፕሪሚየር ሊጉ መቀሌ 70 እንደርታ ከምድረ ገነት ሽሬ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ መቀሌ 70 እንደርታ ከምድረ ገነት ሽሬ ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር በመቀሌ 70 እንደርታ እና በምድረ ገነት ሽሬ መካከል ዛሬ ይደረጋል።
ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች መካከል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 22 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ18 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽሬ በበኩሉ 19 ጨዋታዎችን አከናውኖ በአምስቱ ድል ሲቀናው በስድስቱ ተሸንፏል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 13 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ 13 ጎሎችን አስተናግዷል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ23 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ምድረ ገነት ሽሬ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።