ቀጥታ፡

በዞኑ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገ ድጋፍ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገቡ

ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገ ድጋፍ ሶስት የአምራች ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ወደ ስራ ገቡ።

በዞኑ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በሉማሜ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉነሽ ውበቴ በወቅቱ እንደገለጹት ንቅናቄው ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማነቃቃት አስችሏል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ፣ የተጠናቀቁት ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡና አዳዲስ ባለሃብቶችን በመሳብ ንቅናቄው መልካም እድል መፍጠሩንም አክለዋል።


 

በተደረገው ድጋፍና ክትትል በዛሬው እለት ሶስት መካከለኛና አነስተኛ አምራች ፋብሪካዎችና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ተናግረዋል።

የተመረቁት ፋብሪካዎችም ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደፈጠሩ ጠቁመው የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማነቃቃት እንደሚያስችሉም ገልጸዋል።

ከተመረቁት ፋብሪካዎች መካከልም የዘይት ማምረቻ፣ የወተትና የወተት ተዋጽኦና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲሁም የወተት ፋርም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በንቅናቄው የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ዋለ አባተ እንደገለጹት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የጀርባ አጥንት ነው።


 

በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ከተተገበረ ወዲህ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ፣ የስራ እድሎች እየተፈጠሩ፣ ተኪና የወጪ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በዞኑ ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር ከመፍታት ጎን ለጎን በንቅናቄው በመታገዝ ለባለሃብቶች መሬት በማቅረብ፣ መሰረተ ልማት በማሟላትና ብድር በማመቻቸት ላይ በማተኮር መሰራቱን ተናግረዋል።

የሃፒ የወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ደረስ ውብሸት የወተትና ወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያውን ለመገንባት 230 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በቀን 30ሺህ ሊትር ወተት ከአካባቢው አርሶ አደሮችና ከተደራጁ ማህበራት ተረክቦ በማቀነባበር ቅቤ፣ አይብ፣ እርጎ፣ አይስክሬም፣ ሞዞሬላና ሌሎች ሰባት አይነት ተዋጽኦዎችን ያመርታል ብለዋል።

ፋብሪካው ከ130 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች አዲስ የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው ምርቱን ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች በመላክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ወጣት ሳለው መብሬ እንዳለው በፋብሪካው በተፈጠረለት የስራ እድል በመጠቀም የራሱንና የቤተሰቡን አኗኗር ለመቀየር እንደሚሰራ ተናግሯል።

በዞኑ ወደ ስራ የገቡ አራት ከፍተኛ፣ 49 መካከለኛና 194 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም