በወሰድነው ስልጠና ታግዘን የሚሰጠንን ግዳጅ ለመፈጸም ተዘጋጅተናል-የልዩ ሀይልና ጸረ-ሽብር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በወሰድነው ስልጠና ታግዘን የሚሰጠንን ግዳጅ ለመፈጸም ተዘጋጅተናል-የልዩ ሀይልና ጸረ-ሽብር አባላት
ሀዋሳ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ በወሰድነው ስልጠና ታግዘን የሚሰጠንን ግዳጅ ለመፈጸም ተዘጋጅተናል ሲሉ በመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የልዩ ሀይልና ጸረ-ሽብር ክፍል አባላት ገለጹ።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዠ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የተመሰረተበት 65ኛ ዓመት በዓል በሀዋሳ ተክብሯል።
በስነስርዓቱ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የልዩ ሀይልና የጸረ-ሽብር ክፍል አባላት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ድንበሯን የሚያስከብሩና ሰላሟን የሚያስጠብቁ ጠንካራ ጀግና ሰራዊት አላት።
ጊዜውን መሰረት ያደረገና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ ሀይል ያላት ሀገራችን ምንም የሚበግራት ሀይል የለም ብለዋል።
የልዩ ሀይልና ጸረ-ሽብር ክፍል አባል የሆኑት ምክትል አስር አለቃ አብረሀም ገዛኸኝ እንዳለው፥ ውትድርና የሚወደውና የሚያከብረው ሙያ በመሆኑ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው።
በዕዙ ስር ከመደበኛ እግረኛ አንስቶ እስከ ልዩ ሀይል ድረስ የተለያዩ ግዳጆችን መፈጸም የሚያስችለውን ስልጠና አግኝቷል።
ኢትዮጵያ የብዙ ጀግኖች ወታደሮች እናት ናት ያለችው መሰረታዊ ወታደር ፋንታዬ ንጉሴ በስልጠና ላይ በነበረኝ ቆይታ በቂና ለማንኛውም ግዳጅ ብቁ የሚያደርገኝን ከመሰረታዊ የውትድርና ስልጠና በተጨማሪ የኮማንዶ ስልጠና ወስጃለሁ ብላለች።
እኔ እያለሁ ሀገሬን ጠላት አይደፍራትም፤ በወሰድኩት ስልጠና በመታገዝ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብላለች።
በወሰደችው ስልጠና የሚሰጣትን ግዳጅ በጥንካሬና በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
የልዩ ሀይልና የጸረ-ሽብር ክፍል ባልደረባ የሆነው አስር አለቃ ቾል ቶት በበኩሉ፥ ቀደም ሲል በተለያዩ ግዳጆች ተካፍሎ እንደነበርና አሁን በልዩ ሁኔታ ስልጠና በመውሰድ ኮማንዶ መሆን እንደቻለ ገልጿል።
ሀገር ከሌለ እኔም የለሁም፣ ሀገር ማለት ህይወቴም ደሜም ነው ያለው አስር አለቃ ቾል፥ በርካታ የስልጠና ሂደቶችን በማለፍ ዛሬ ላይ እንደደረሰና በወሰደው ስልጠና በመታገዝ ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሰልጣኞች በወሰዱት ስልጠና ለሀገርና ለህዝብ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው በየብስ፣ በአየርና በባህር ማንኛውንም ግዳጅ ለመፈጸም የሚያስችላቸውን አቅም እንደገነቡ ተናግረዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከየካቲት 7 ጀምሮ በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር፣ በወታደራዊ ትርኢትና ሌሎች መርሀ ግብሮች ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የማጠቃለያ ፕሮግራም ተከናውኗል።
በዛሬው መርሃ ግብር የሰራዊቱ 44ኛ ኮርስ የኮማንዶ ምሩቃን ቀይ ቦኔታቸውን በመልበስ በይፋ የተመረቁ ሲሆን የክብር እንግዶች በተገኙበት የልዩ ዘመቻዎች እዝ የሰራዊቱ አባላት የወታደራዊ የሰልፍ ስነ ስርአት ተከናውኗል።