ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖረው ዕድል የከፈተ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አካታችነትን መሰረት በማድረግ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖረው የበለጠ ዕድል የከፈተ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ማስረከብ መቻሉንም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል የምክክር አውድ ለመፍጠር በወሳኝ የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

የምክክር ሂደቱም ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነትን በማጽናት ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ መድረክ ላይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ ልማት ለማፋጠን በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ቁልፉ መሳሪያ ኢትዮጵያውያን ተወያይተን ልንፈታቸው በሚገቡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወያያ መድረክ ለመፍጠር የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ወደ ውጤት በመቀየር ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ ኮሚሽኑ ብሄራዊ ምክክሩን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር እስካሁን ባለፈባቸው ምዕራፎች የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል። 

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች አካል ጉዳተኞች በንቃት እንዲሳተፉ የማድረግና አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ የማስረከብ ስራዎች ከተከናወኑ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ፌዴሬሽኑ አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በዋናው የሀገራዊ ምክክር ላይ የሚሳተፉ አካል ጉዳተኞች ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መለየታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለስምንት ወራት ማራዘሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም