በሰራዊታችን ጠንካራ ቁመና እና ዘመናዊነት ክብርና ኩራት ተሰምቶናል-የሀዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሰራዊታችን ጠንካራ ቁመና እና ዘመናዊነት ክብርና ኩራት ተሰምቶናል-የሀዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች
ሀዋሳ፤የካቲት 15/1018(ኢዜአ)፦በሰራዊታችን ጠንካራ ቁመና እና ዘመናዊነት ክብርና ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ የሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ ትጥቅ የተሟላና የሀገሩን ክብርና ዳር ድንበር ለማስከበርና ለየትኛውም ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ጀግና፣ብቁና ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን መገንዘባቸውን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የምሥረታ በዓሉ ታዳሚ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የሀገር መከታ በሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ትዕዛዙ ሂርጶ በዓሉ በሀዋሳ ከተማ መከበሩ በከተማዋ ከተገነባው የኮሪደርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር ተደምሮ ልዩ ድምቀት ለከተማዋ እንደሰጣት ጠቅሷል፡፡
የዕዙ የሰራዊት አባላት ባሳዩት ትርኢት የሀገር መከታና አለኝታ መሆናቸውን ማስመስከራቸውን ተናግሯል፡፡
በመሆኑም በመከላከያ ሰራዊታችን እጅግ ኮርተናል ነው ያለው፡፡
ወጣት ሶፊያ ሸንቁጤ በበኩሏ በአካል ተገኝታ ወታደራዊ ትርዒት ስትመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገልፃ፥ የጀግንነት ተግባራቸው በኢትዮጵያዊነቷ ደስታ እንዲሰማት እንዳደረጋት ነው ያስረዳችው፡፡
የሀገራችንን ዳር ድንበር ከማንኛውም ወራሪ ኃይል የሚጠብቁት ወታደሮቻችን ናቸው ያለችው ወጣት ሶፊያ፥በብቃታቸው ኩራት እንደተሰማት ተናግራለች፡፡
በሚያስፈልገው ሁሉ ሰራዊቱን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቁማለች፡፡
አቶ በቀለ ፋሬሶ ደግሞ ወታደሮች የሀገራችንን ዳር ድንበር እንዳይደፈር የሚጠብቁ በመሆናቸው ከነርሱ ጋር በመሆን በዓሉን ማክበራቸው እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፥ በሰራዊቱ ዝግጁነትም እንደኮሩ አስረድተዋል፡፡
ጥንትም በጠላት ያልተደፈረች ኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነቷን ለመጠበቅ ከጀግናው ሰራዊት ጎን እንደሚቆሙም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡