ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል የማድረግ እንቅስቃሴ

አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል የማድረግ እንቅስቃሴ

በጎ አድራጎት ያለምንም ክፍያና ጎትጓች ለህሊና እርካታ ለሰዎች የሚከወን የዕለት ተዕለት ተግባር ነው። 

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል በማድረግ በቤት እድሳት፣ በደም ልገሳ፣ ማዕድ በማጋራትና በሌሎች ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከፕሎጊንግ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በእንጦጦ ፓርክ ያዘጋጀው የጽዳትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ተካሂዷል። 


 

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት በጎ ፈቃደኝነት ለራስ የህሊና እርካታን ከመስጠት ባለፈ፣ ጠንካራና የተሳሰረ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁልፍ ሚና አለው። 

የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ተግባር የዜጎች የዘወትር ባህል ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፤ በዚህም በከተማዋ በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡።

በአሁኑ ወቅት በሙያቸውና በጉልበታቸው ለሀገራቸው ለህዝባቸው የሚደርስ ማህበረሰብ መፍጠር መቻሉን አንስተው፤ ይህ ንቁ ትውልድ የመፍጠር ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

እንደ ፕሎጊንግ ኢትዮጵያ  ሁሉ ህብረተሰቡም ሆነ ሌሎች አካላት ብዙ ጥቅም በሚያስገኘው በጎ ፍቃድ  በመሳተፍ ሀገሩንና ወገኑን ማገልገል ይገባዋል ብለዋል፡። 

የፕሎጊንግ ኢትዮጵያ መስራች ፕሮፌሰር ፍሬው ከፍያለው በበኩላቸው፤ አካባቢን መንከባከብ የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ድርጅታቸው ላለፉት አምስት ዓመታት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከጽዳት ጋር በማቀናጀት (Plogging) በየሳምንቱ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን የመሰብሰብ ዘመቻ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል። 

ዝቅ ብሎ ቆሻሻን ማንሳት ለራስ ክብርንና ከፍታን ይሰጣል ያሉት ፕሮፌሰሩ ማህበረሰቡ ይህንን ልምድ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።


 

በዕለቱ በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት በጎ ፈቃደኞች ፍቅር ግርማ እና ካሱ መገርሳ በሰጡት አስተያየት፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በመሳተፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፤ በቀጣይም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም