ቀጥታ፡

ሀዋሳ የፍቅር፣የሰላም፣ የደስታ ከተማ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያ ራዕይ የሚፈልቅባት ከተማ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታ ከተማ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያ ራዕይ የሚፈልቅባትና የሚነገርባት ከተማ ናት ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ገለጹ።

መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ከአምስት ዓመት በፊት አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ ትሆናለች መባሉን አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በርካታ ከተሞች አበባ ሆነዋል ብለዋል።

ሀዋሳ ደግሞ ብርሃን ሆና ስላየናት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሀዋሳ ተሞሽራለች የሀዋሳን ብርሃን፣ የህዝቡን ፍቅር ታሪካዊ ማንነቱን እየመጣቹ እንድትጋሩ ግብዣ አቅርቤላችኋለው ሲሉም ተናግረዋል።

በዚች ከተማ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ማረጋገጥ የምፈልገው የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ይሆናል፤ የኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪነት እና ምሳሌነትን እናረጋግጣለን ብለዋል።

ልጆቻችንም ድህነትን ታሪክ በማድረግ ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን እናስረክባለን ብለዋል።


 

ላባችንን አንጠፍጥፈን፤ ደማችንን አፍስሰን፣ አጥንታችንን ከስክሰን፣ኢትዮጵያን እንገነባለን፣ ሲዳማን እንገነባለን፣ሀዋሳ እንገነባለን፤ አፍሪካን እንገነባለን ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ምርጥ ከንቲባ አግኝተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ውቢቷን ሀዋሳ ዳግም በመስራት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመጣባት የሚጓጓ ዓለም አቀፍ ከተማ እንድትሆን ከከንቲባው፣ ከርእሰ መስተዳድሩ ጎን በመቆም ሀዋሳን ዳግም እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም