ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ጥረት ለቀጣናው ሀገራት የጋራ እድገትና ብልጽግና ሁነኛ መሰረት የሚያኖር ነው

ሆሳዕና፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ጥረት ለቀጣናው ሀገራት የጋራ እድገትና ብልጽግና እንደሚያመጣ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተለይም ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ የጋራ ልማትንና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው።
 
በዚህም መሰረት በሰላም ማስከበርና ሽብርተኝነትን መከላከል እንዲሁም የኤሌክትሪክ ሃይልን ጨምሮ በሌሎች መሰረተ ልማቶች የጋራ ትስስር በመፍጠር ጠንካራ አህጉራዊ መሰረት እንዲኖር በመስራት ላይ ትገኛለች።
 
በአህጉሩ ሁለንተናዊ ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን ሚና በተመለከተ ኢዜአ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን አነጋግሯል። 
 
በዩኒቨርሲቲው በሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ፤ በአፍሪካ በሁሉም ረገድ የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።
 
በቀጣናዊ የልማት ትስስር፣ በሃይል ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ተጨባጭ ውጤት የተገኘባቸው ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው በዚህም ለአጀንዳ 2063 ግብ መሳካት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን አስረድተዋል።
 
የኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት በጉልህ እየታየ መምጣቱን ጠቁመው በቀጣናው የተደማጭነትና የተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅሟ እያደገ ስለመምጣቱም ተናግረዋል።
 
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህሩ ፈቃዱ ኤርሱሞ፤ ኢትዮጵያ በተለይም በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፉ እመርታዊ ለውጥና ማንሰራራት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
 
በዲጂታል ልማትና በቱሪዝም ዘርፉ በጥቂት አመታት ውስጥ የላቀ ውጤት መመዝገቡን አንስተው የእነዚህ ድምር ውጤት ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግብ ስኬት ሁነኛ መሰረት እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
 
በአፍሪካ አህጉራዊ ትስስርንና የትብብር ግንኙነትን ለማጠናከር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ጠቁመው በተለይም ጎረቤት ሀገራት እድገቷንና ፍላጎቷን መሰረት ባደረገ መልኩ ትብብርና አብሮነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም