ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ፣ አጥንትና ደም ትሰራለች፤ ለልጆቻችንም በክብር እናሸጋግራታለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ሀዋሳ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ፣ አጥንትና ደም ትሰራለች፤ ለልጆቻችንም በክብር እናሸጋግራታለን ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር የማጠቃለያ ፕሮግራም በሀዋሳ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

በመርሃ ግብሩ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የእኛ ተልእኮና ራእይ ለትውልድ የሚሸጋገር ሁነኛ ተቋም መገንባት ነው ብለዋል።

በዚህም የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ በድል የሚያውለበልብ ጀግና እና ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ፣ አጥንትና ደም ትሰራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ሳትደፈር በክብርና በነፃነት ለልጆቻችን እናሸጋግራታለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ የሚሰራ በአእምሮም ይሁን በአካል ብቃት ዝግጁ የሆነ ጦርነትን፤ በአጭር መቋጨት የሚችል ጠንካራ እና አስተማማኝ ሰራዊት ገንብታለች ነው ያሉት።

የአየር ወለድ አባላት የሀገር ኩራት የሆኑ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጆች መሆናቸውን አንስተው በአንደኛው ክንፍ አላማ በሌላኛው ክንፍ ደግሞ ዲስፕሊን አንግበው የቆሙ ጀግኖች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል። 

የእኛ ተልእኮና ራእይ ለትውልድ የሚሸጋገር ሁነኛ ተቋም መገንባትና የአፍሪካን ሰላም ማረጋገጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። 

በመሆኑም የእናንተ ተልእኮ ኢትዮጵያን መገንባት፣ መጠበቅ፣ ማጽናትና ማሸጋገር መሆን አለበት በማለትም በአጽንኦት አስገንዝበዋል። 

የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር የማጠቃለያ ፕሮግራም፤ የሰራዊቱ 44ኛ ኮርስ የኮማንዶ ምሩቃን ቀይ ቦኔታቸውን በመልበስ በይፋ የተመረቁ ሲሆን የልዩ ዘመቻዎች እዝ የሰራዊት አባላቱ ወታደራዊ ትርዒት አከናውነዋል።
 
የሰራዊቱ አባላት ልዩ ግዳጆችን በአጭር ጊዜ ለመፈፀም በሄሊኮፕተር የአየር ላይ ዝግጁነትን ኮማንዶዎች ደግሞ የውጊያ ስልቶችን አሳይተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም