ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት የሚያስጠብቅ ጀግና የህዝብ ልጅ ነው-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት የሚያስጠብቅ ጀግና የህዝብ ልጅ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

65ኛው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምስረታ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ስርዓት "የማይበገር ጽናት፤ የማይታጠፍ ማንነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሃዋሳ ስታዲየም በታላቅ ድምቀት ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉበኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች፣ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣቹህ መልዕክት፤ የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እያስጠበቀ የሚገኝ ጀግና የህዝብ ልጅ ነው ብለዋል።

የህዝብ ልጅ የሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊትም በተለያዩ ጊዜያት የሚቃጡ ጥፋቶችን በማክሸፍ አኩሪ ገድል እየፈጸመ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዜጎች ሰላም፣ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት አንድነት መከታና የመጨረሻ ምሽግ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሠራዊት አባላትም የተለየ ሀገራዊ ተልዕኮን በብቃት የሚፈጽሙ ጀግኖች መሆናቸውን አንስተዋል።

የሲዳማ ክልል መንግስትና ህዝብም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በሚያስፈልግበት ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች 👉 https://linktr.ee/ENADigital

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም