የኢትዮጵያን፣የቀጣናውንና የአፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ኤሊት ፎርስ ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን፣የቀጣናውንና የአፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ኤሊት ፎርስ ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጣናውንና የአፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ኤሊት ፎርስ ተገንብቷል ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሰው ልጅ ከሀገሩ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ተጋርቶ ይወለዳል።የዛሬ አየር ወለዶች ደግሞ ከእናት ከአባታቸው፣ ከኢትዮጵያ ሀገራቸው እንዲሁም ከአየር የተወለዱ የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታዎች ናቸው ብለዋል።
ቀይ ቦኔት የለበሱ ከአየር ተምዘግዝገው የሚወርዱ ባለ ሁለት ክንፍ ልዩ አየር ወለዶቹ በአንደኛው ክንፍ ዓላማ በሌላኛው ክንፍ ዲሲፕሊን ያነገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ውጊያ የሚያስቀሩና ውጊያ የሚጨርሱ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃችንን በድል የሚያውለበልቡ ጀግኖች መሆናቸውን አመልክተው፤ ለእነዚህ ጀግኖች የሚገባቸውን ክብር እንደሀገር በጋራ ሰጥተዋል።
የኛ ተልዕኮ ራዕይ ያለው፣ለትውልድ የሚሸጋገር ሁነኛ ተቋም መፍጠር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተልዕኳችን ውጊያ የሚያስቀርና የሚጨርስ ኤሊት ፎርስ መገንባት ነው ብለዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አባላት ተልዕኮ ኢትዮጵያን መገንባት፣ኢትዮጵያን መጠበቅ፣ ኢትዮጵያን ማጽናትና ኢትዮጵያን ማሸጋገር መሆኑንም በአፅንኦት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ትሰራለች፤ በልጆቿ አጥንትና ደም ትጸናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ሳትደፈር በክብር እና በነፃነት ለልጆቻችን የምናሻግራት ብቸኛዋ የአፍሪካ ፈርጥ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዝግጅታችን በድፍን አፍሪካ ሰላም እና ብልጽግናን ለማረጋገጥና በቀጣናው ላሉ ሀገራት አለኝታ መከታ ጋሻ ለመሆን ነው።
በዚህ ብቻ ሳያበቃ ወንድም ህዝቦችን በመደገፍ ከሱማሌ ጫፍ እስከ ምፅዋ ጫፍ በባህር ላይ የሚያጋጥሙ ሽብሮችን ለማስቀረትና ልማትና ብልጽግናን በቀጣናው ለማረጋገጥ እንሰራለን ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው በቂ የሆነ ኤሊት ፎርስ፣ ቴክኖሎጂን የታጠቀና የሚጠቀም፣ በምሽግ ብቻ ሳይሆን በስትራቴጂክ ቦታዎች ውጊያን የሚያሳጥር ተቋም መገንባቱን አስታውቀዋል።
በዚህም ድፍን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ብሎም የአፍሪካ ሀገራት እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ኤሊት ፎርስ የምንገነባው በቀጣናችን ውጊያና ሽብር እንዳይፈጠር መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሲፈጠርም ባጠረ ጊዜ ለመቋጨት በማለም ነው ብለዋል።
የገነባነው ሃይል ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ዓለም አቀፍ ስምሪቶች ስመጥር ተግባራት ሲፈጽም እንደኖረው ሁሉ በዚህም ዘመን ያንን ታሪክ የሚደግም የቀይ ቦኔት ክብር፣ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር፣ ለሀገር ክብርና ለሀገር ነፃነት እራሱን የሚሰዋ ብቁ ሠራዊት መሆኑን ተናግረዋል።
በአእምሮም በአካልም የበለፀገ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፣ውጊያን የሚሰራና የሚጨርስ ኃይል መገንባቱን በማንሳት፥ የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ነፃነት የአፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ኃይል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች
https://linktr.ee/ENADigital