ሁለገብና አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት ገንብተናል-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለገብና አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት ገንብተናል-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦በብዛት፣በጥራት የሰለጠነ ሁለገብና አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ የምስረታ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ስርዓት "የማይበገር ጽናት፤ የማይታጠፍ ማንነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሃዋሳ ስታዲየም በታላቅ ድምቀት ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች፣ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ከውጪም ከውስጥም የተጋረጡባትን ፈተናዎች በመመከት በኩል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ ገድል ፈጽሟል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በሪፎርም ጠንካራ ሀገራዊ ሰራዊት መገንባቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማንም ውግንና የሌለው ሀገራዊ ሰራዊት እንዲገነባ በሰጡት አመራር መሰረት የሰራዊት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መምጣቱን አንስተዋል።
በጦርነት ውስጥ የሰራዊት ግንባታ እየተሰራ እንደመጣ ገልጸው፤ ያልተዘጋጀ ፈርሶ የነበረ ሰራዊትን በመገንባት እዚህ ደረጃ መድረሳችን ተዓምር ነው ብለዋል።
በዚህም በጦርነት የተፈተነና በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሰለጠነ ሠራዊት መገንባቱን ጠቁመው፤ ልዩ ልዩ የሰራዊት ክፍሎች እና ዕዞች ግንባታ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየአካባቢው የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን ጠቁመዋል።
ከጦርነት በኋላም 7/24 በመስራት የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት በመስራት የሰራዊት ግንባታ ተልዕኮ ለማሳካት በብዛት፣በጥራት በአደረጃጀት በዓይነት በቴክኖሎጂ፣በመከላከያ ኢንዱስትሪ ልማትና በመሰረተ ልማት ሁለገብ የሆነ አስተማማኝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገንብተናል ብለዋል።
ዕዙ ሀገርንና ህዝብን ያኮራ ጠንከራ ሰራዊት መሆኑን ገልጸው፤ ዕዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስልጠና ጥራቱን በማሳደግ ኃይል ከማባዛት ባለፈ ሪፐብሊካን ጋርድን አምጦ የወለደ የጦር ክፍል ነው ብለዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ባለፉት 65 ዓመታት በበርካታ አካባቢዎች በተካሄዱት ጦርነቶች ውጊያ ቀያሪ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም 44ኛ ዙር መሰረታዊ ኮማንዶ ሲሰለጥኑ የነበሩ ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸው፥ በዕዙ ምስረታ ቀን ላይ ልዩ እንደሚያደርግ ገልጸው፥ ለተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ በሚያስችል ሁኔታ ሰራዊቱ አሁን የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።