ቀጥታ፡

የሀገሩን ክብርና ዳር ድንበር ለማስከበር ለየትኛውም ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ጀግና፣ብቁና ጠንካራ ሰራዊት ገንብተናል-ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

ሀዋሳ፤የካቲት 15/2018 (ኢዜአ)፦የሀገሩን ክብርና ዳር ድንበር ለማስከበር ለየትኛውም ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ጀግና፣ብቁና ጠንካራ ሰራዊት ገንብተናል ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።

የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር የማጠቃለያ ፕሮግራም፤ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና ሌሎችም የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የሰራዊቱ አባላትና ሌሎችም በተገኙበት በሀዋሳ ስታዲየም ተከብሯል።


 

በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሰራዊት እንገነባለን ባሉት መሰረት የሰራዊት ግንባታውን በላቀ መልኩ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂም ይሁን በትጥቅ በእጅጉ የተሟላ መሆኑን በማንሳት የሀገሩን ክብርና ዳር ድንበር ለማስከበር ለየትኛውም ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ጀግና፣ ብቁና ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ የልዩ ዘመቻዎች እዝ በሁሉም ረገድ የተደራጀና የተዘጋጀ እዝ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ በፊት የተከናወኑ በርካታ ጀብዱዎችን ዘርዝረዋል።

በለውጡ ሂደት ነውጥ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ አካላትን ተከታትሎ ህግ በማስከበር አሸናፊ በመሆን በድል መወጣት መቻሉን ተናግረዋል።

ክብረ በዓሉ በአየር ላይ ትርኢት፣ የውሃ ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም በምድር ወታደራዊ ጥበቦች ታጅቦ ሲከበር የቆየ ሲሆን በዛሬው እለት የማጠቃለያ ፕሮግራም ተከናውኗል።


 

በዛሬው መርሃ ግብር የሰራዊቱ 44ኛ ኮርስ የኮማንዶ ምሩቃን ቀይ ቦኔታቸውን በመልበስ በይፋ የተመረቁ ሲሆን የክብር እንግዶች በተገኙበት የልዩ ዘመቻዎች እዝ የሰራዊቱ አባላት የወታደራዊ የሰልፍ ስነ ስርአት ተከናውኗል።

የሰራዊቱ አባላት ልዩ ግዳጆችን በአጭር ጊዜ ለመፈፀም በሄሊኮፕተር የአየር ላይ ዝግጁነት አሳይተዋል።

ከሀዋሳ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች በህብረት የተለያዩ ትርኢቶችን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም