ቀጥታ፡

የውጊያ ማርሽ ቀያሪና የሀገር መከታ የሆነው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦ የውጊያ ማርሽ ቀያሪና የሀገር መከታ የሆነው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በመንግሥትና በሕዝብ የሚሰጠውን ግዳጅ በየትኛውም የመሬት ገፅና ሁኔታ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በዚህ ወቅት እንዳሉት በዓሉ ባለፉት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎቹ መፅሐፍ፣ አዲስ አርማ፣ የዕዙ መዝሙርና ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅተው መመረቃቸውን አንስተዋል።

የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫና የተለያዩ ትርኢቶች ለበዓሉ ድምቀት ቀርበዋል ነው ያሉት።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ማክበር ያስፈለገው በሦስት ዋና ምክንያቶች መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

አንደኛው በሠራዊቱ ሪፎርም የ65 ዓመት ጉዞን ለቀጣይ ትውልድ በሚጠቅም መልኩ ደምረን በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለተኛው በሪፎርሙ የሥራ ውጤት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አሁን ያለበትን ቁመና ለህዝብ፣ ለመንግሥትና ለሀገር መከታ፣ ለጠላት ደግሞ መቅሰፍት መሆናችንን በማሳየት አርፈው እንዲቀመጡ፣ ያን ካላደረጉ ግን ውጊያ ጨራሽ መሆናችንን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በሶስተኛነት ሲጠቅሱም ጀግንነት ትናንት ነበረ፣ ዛሬም ቀጥሏል፤ በትናንት ስልት መሄድ አንችልምና የትናንቱን ልምድ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አዋህደን ከዝግጅቱ ልምድ ለመቅሰም በማለም እየተከበረ ነው ብለዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከአንድ ሻምበል ተነስቶ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የበቃው ብዙ ውጣ ውረዶችን በማለፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአንድ እጅ እየተዋጋን በሌላ እጅ እያሰለጠንን የልዩ ዘመቻዎች ዕዝን ከማደራጀት ባለፈ ጠንካራና የሀገሪቱ ከፍተኛ መቺ ሃይል የሆነ የሪፐብሊካን ጋርድ ኃይል እንዲመሰረት መደረጉን ጠቅሰዋል።


 

በዛሬው ዕለትም 44ኛ ዙር መሰረታዊ ኮማንዶ ሲሰለጥኑ የቆዩ ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸውን ጠቅሰው፣ በርካታ አባላትም በስልጠና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ከትናንትና የበለጠ የተደራጀ የሰለጠነ ውስጣዊ አንድነቱ ከላይ እስከ ታች የዳበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህርም በየብስም በየትኛውም አየር ፀባይና የመሬት ገጽ የውጊያ ማርሽ ቀያሪነታችንንና የምድር ድሮንነታችንን በማስቀጠል መንግስታችን፣ ተቋማችንና ህዝባችን ለሚሰጡን ማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ ነን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም