ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን የተጎናጸፈች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትምህርት የሚሆን አኩሪ ገድል ነው

አዲስ አበባ የካቲት 15/2018(ኢዜአ)፦የዓድዋ ድል ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን የተጎናጸፈች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትምህርት የሚሰጥ አኩሪ ገድል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የቅኝ ግዛትን ምኞት ለማክሸፍ ከአራቱም አቅጣጫ የተመሙ ቅድመ አያቶች የጥቁር ህዝቦች ነፃነትና የኩራት ምንጭ የሆነው የዓድዋ ድል ለመቀዳጀት በቅተዋል።

በየካቲት 23/1888 ዓ.ም የኢትዮጵያዊያን ሕብረብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠበት የዓለም ጭቁን ህዝቦች የነፃናት ብርሃን የተተለመበት የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ ይከበራል።

የአዲሰ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ 130ኛውን የዓድዋ ድል ምክንያት በማድረግ ”የዓድዋ አደራ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አካሂዷል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካን ጨምሮ ተጋባዦች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የዓድዋ ድል የቅድመ አያቶች አብሮነት፣ አንድነትና አይበገሬነት ተሰናስለው ያስገኙት የጥንካሬና የጽናት ውጤት ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድልም ኢትዮጵዊያን በሀገራቸው ሉዓላዊ አንድነት ላይ የሚቃጡ ችግሮችን መቀልበስ የሚችሉ የማይበገሩ ህዝቦች መሆናቸውን ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅድመ አያቶች በዓድዋ ድል የተቀዳጁት የዓድዋ ድልም የአሁኑ ትውልድ በልማትና በዘላቂ ሰላም በመድገም የተሟላ ሉዓላዊነት የተጎናጸፈች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የዓድዋ ድል ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን የተጎናጸፈች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትምህርት የሚሆን አኩሪ ታሪክ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ተራ የጦርነት ማሸነፊ ውጤት ሳይሆን ፅናት፣ ብልሃት፣ ጥበብና የአንድነት ብቃት ውጤት ነው ብለዋል።

ቅድመ አያቶች በፍጹም አንድነት ውጣ ወቅረድን በብቃት በመወጣት የተቀዳጁት አኩሪ ድልም በፅኑ ወኔና በጠንካራ አካል ብቃት መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል የአንድነት፣ አብሮነትና የጽናት ትምዕርት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በማህበረሰብ ስፖርትም የታየውን አንድነት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና መድገም እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም