ቀጥታ፡

ተጠባቂው የቶተንሃም ሆትስፐርስ እና አርሰናል የሰሜን ለንደን ደርቢ ፍልሚያ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/ 2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከአርሰናል ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሊጉ 26 ጨዋታዎች አድርጎ በሰባቱ ሲያሸንፍ በ11ዱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 36 ግቦችን በ26ቱ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር 37 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ስፐርስ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። 

አርሰናል በሊጉ እስከ አሁን ካከናወናቸው 27 ጨዋታዎች 17 ቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። ሰባት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 52 ግቦችን ሲያስቆጥር 20 ጎሎችን አስተናግዷል። 

አርሰናል በ58 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል። 

የሰሜን ለንደኖቹ አርሰናል እና ቶተንሃም ሆትፐርስ 129 ዓመታትን ያስቆጠረ የተቀናቃኝነት ታሪክ አላቸው።

ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙነት እ.አ.አ በ1896 ሲሆን በወቅቱ ዩናይትድ ሊግ በሚባለው የውድድር ፎርማት ላይ ተጫውተው አርሰናል (በወቅቱ አጠራሩ ዎልዊች አርሰናል) ቶተንሃም ሆትስፐርስን 2 ለ 1 አሸንፏል።

እ.አ.አ በ1897 በዩናይትድ ሊግ ተገናኝተው ቶተንሃም ሆትስፐርስ 3 ለ 2 በማሸነፍ በአርሰናል ላይ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

ቡድኖቹ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው ተቀናቃኝነታቸው እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 212 ጊዜ ተገናኝተዋል። 

በዚህም አርሰናል 90 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ቶተንሃም ሆትስፐርስ 67 ጊዜ አሸንፎ 55 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ 67 ጊዜ ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አርሰናል 28 ጊዜ ሲያሸንፍ ቶተንሃም ሆትስፐርስ 15 ጊዜ ድል ቀንቶት 24 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው አርሰናል አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

አርሰናል ካሸነፈ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል። 

ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል። 

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በኤምሬትስ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል 4 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። 

የ43 ዓመቱ ፒተር ባንክስ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌሎች መርሐ-ግብሮች ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊቨርፑል፣ ክሪስታል ፓላስ ከዎልቭስ እና ሰንደርላንድ ከፉልሃም በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም