ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤የፖለቲካ ፓርቲዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያዘጋጀውን የዕጩዎች የስነ ምግባር ደንብ ፈርመዋል።፡፡


 

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።

መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ለይተው እንዲመርጡ የሚያስችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶች ዛሬ ይፋ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ቀጣዩን የመራጮች ምዝገባ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የምርጫ አስፈጻሚዎችና መራጮችን ለሚያስተምሩ 169 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበው፤ በተለይም መገናኛ ብዙኃን ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍትሃዊነት በማስተናገድ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ቦርዱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፈረሙት የሥነ-ምግባር ደንብ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

በዚህም ደንቡ ዋና ዋና የዲሞክራሲ መርሆዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በማንኛውም የቅስቀሳ ወቅት መደለያ ከመጠቀም ወይም ኃይልን መሠረት ካደረገ እንቅስቃሴ መቆጠብ ግዴታ ነው ብለዋል።

የዜጎችን ሰላም የሚያናጋ፣ ግጭት የሚቀሰቅስ ወይም ለአመጽ የሚጋብዝ ንግግር ማድረግ ፍጹም የተከለከለ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከቦርዱ ዕውቅና ውጭ የምርጫ ውጤት ትንበያ መሥራት የተከለከለ ሲሆን፤ ማንኛውም ቅሬታ ያለው አካል በሕግ የተቀመጡ አሰራር ሥርዓቶችን ብቻ የመከተል ግዴታ አለበትም ብለዋል።

በዛሬው መርሃ ግብር ላይ የቦርዱ የሥራ አመራር አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ ሁሉም አካላት ለምርጫው ስኬታማነት በጋራ ለመሥራት ስምምነታቸውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም