ቀጥታ፡

በመርሃ ግብሩ ታቅፈን በትጋት ሰርተን በመቆጠባችን ከተረጂነት ለመውጣት ችለናል-ተጠቃሚዎች

ድሬደዋ ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-  በሴፍትኔት መርሃ ግብር ታቅፈው በትጋት ሰርተው በመቆጠባቸው ከተረጂነት ለመውጣት መቻላቸውን የድሬዳዋ የሚገኙ ሴት የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

በከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪት እንዲያፈሩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

የሴፍትኔት ፕሮግራም በከተሞች የሚታየውን ሥራ አጥነትና ስር የሰደደ ድህነት በመቀነስ በኩልም የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የተለያዩ ተጠቃሚዎች ይገልፃሉ ።

መርሃ ግብሩ በከተሞች ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን በሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸውና የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው።  

በድሬዳዋ አስተዳደር የሴፍትኔት ተጠቃሚ የነበሩ ሴቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሴፍትኔት መርሃ ግብሩ ጠንክረው በመስራትና ጥሪት በመቋጠር ወደ ሌሎች የልማት ስራዎች ለመሻገር መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ማስቻሉን አመልክተው ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመውጣት የራሳቸውን መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንደቻሉ በመጠቆም።

በመርሃ ግብሩ በመታቀፍ ከተረጂነት ለመውጣት እንደቻሉ የተናገሩት ወይዘሮ እታገኝ በለጠ እና ወይዘሮ አበባ ኃይሌ እንዳሉት፤  በሴፍትኔት መርሃ ግብር ታቅፈን በትጋት በመስራታችን  ከተረጂነት ለመውጣት ችለናል።


 

በተለይ ለሴቶች በንግድ ስራና በክህሎት ማሳደግ ላይ የተሰጠው ስልጠና አዋጪ በሆነ የገቢ ማግኛ ስራ ላይ በመሰማራት ከተረጂነት ለመውጣት ያስቻለና ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር እድልንም ፈጥሮልናል ብለዋል።

መንግስት ተግባራዊ ባደረገው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር በመሳተፍ ባገኘሁት ድጋፍና ስልጠና ራሴን ከመቻል ባለፈ የቁጠባ ሒሳብ ለመክፈትና ገንዘብ ለማስቀመጥ  ችያለሁ ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ከዲጃ ኢብሮ ናቸው።


 

ከዚህ ባለፈም  ልጆቻቸውንም በተገቢው መንገድ ለማስተማር መቻላቸውንም ነው የገለፁት።


 

በድሬዳዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት የከተማ ምግብ ዋስትና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መድህኔ፤ መንግስት  ተረጂነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት በውጤት እየታጀቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፍና የሙያ ስልጠናዎች በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ወደ አምራችነት እያሸጋገሩ መሆናቸውን በመግለፅ።

በድሬዳዋ ከተማም በሴፍትኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ 340 የሚደርሱ ሴቶች በቆጠቡትና በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ  በመታገዝ በተለያዩ የገቢ ማግኛ ስራዎች ላይ በመሰማራት ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም