ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማቱ የሰሜን ሸዋ ዞን ከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል

ደብረ ብርሃን ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-የኮሪደር ልማቱ የሰሜን ሸዋ ዞን ከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠሩ ተመላከተ፡፡

በኢትዮጵያ በከተማና ገጠር እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ እያዘመነ ነው። 

የኮሪደር ልማቱ የከተሞችን ውበት ከመግለጥ ባለፈም ለዜጎች ዘመናዊ መሠረተ ልማትን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞችን ለቱሪዝም፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጓቸው መሆኑም ተገልጿል።

የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘላለም መኮንን፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጋት ነው ብለዋል።


 

በከተማዋ ባለፈው ዓመት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የመሸጋገሪያ ድልድይ፣ የጎርፍ መቀልበሻ ካናልና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ያካተተ አንድ ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው ዓመትም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የእግረኛ መንገድ፣ የመንገድ ዳር መብራትና ሌሎች ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን በማዘመን ሳቢና ውብ ከማድረጉ ባለፈ፣ በግንባታው ሂደት ለ500 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማቱ ዜጎች መንገድ፣ መብራትና ቴሌኮምን የመሳሰሉ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ማድረጉንም አመልክተዋል።


 

የሰሜን ሸዋ ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ ብርቃብርቅ ተሾመ በበኩላቸው፤ በኮሪደር ልማት የሸዋ ሮቢትን ተሞክሮ በመውሰድ ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በለሚ፣ በአለም ከተማ፣ በአረርቲና በቡልጋ ከተሞች የ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እንደ አቶ ብርቃብርቅ ገለጻ፣ የኮሪደር ልማቱ በዞኑ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስህቦችን ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው።

የሸዋ ሮቢት ነዋሪዋ አሰገደች ኃይለስላሴና የዓለም ከተማ ነዋሪው አካሉ ደጀን፤ የኮሪደር ልማት ስራዎቹ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለነዋሪዎች አዲስ የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

ልማቱ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ተከትሎ ቀሪ ሥራዎችም በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም