ቀጥታ፡

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል

አምቦ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-የአስጎሪ -ደንዲ- ኮቶባ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው ተመላከተ፡፡

የአስጎሪ -ደንዲ- ኮቶባ የኮንክሪት አስፋልት  መንገድ ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።


 

እየተገነባ ያለው የኮንክሪት አስፋልት መንገድም በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋን እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖችን እንደሚያገናኝም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የአምቦ አካባቢ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ አለሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ የአስጎሪ -ደንዲ- ኮቶባ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው።


 

ፕሮጀክቱ በ2017 በጀት ዓመት መጀመሩን ገልጸው፣ በውሉ መሰረት በ2019 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

መንገዱ 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን የፌዴራል መንግስት በመደበው ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።

በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የአስጎሪ-ደንዲ-ኮቶባ መንገድ ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ለሊሳ ጉዲሳ፤ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ አጠናቀን ለማስረከብ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ በጥራትና በፍጥነት ሌት ተቀን እየሰራን ነው ብለዋል።


 

የፕሮጀክቱ ግንባታም የአካባቢውን ነዋሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአስጎሪ-ደንዲ-ኮቶባ መንገድ ተጠሪ መሀንዲስ ሽመልስ ገመቹ በበኩላቸው፤ የመንገዱ ግንባታ አሁን ላይ ከ45 በመቶ ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል። 


 

በግንባታው ሂደት የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ይህም ስራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የደንዲ ወረዳ ነዋሪ አቶ ቤለማ አኩማ በበኩላቸው፤ በመንገዱ ግንባታ ለበርካታ ዓመታት የአስፋልት መንገድ ይገንባ ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘቱን አንስተው፣ ይህም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች የምርት ማሳደጊያ ግብዓትና የግብርና ምርታቸውን የሚያጓጉዙት በጋማ እንስሳት መሆኑን ጠቅሰው፤ የመንገዱ መሰራት ከዚህ ችግር እንደሚያሳርፋቸውም ገልጸዋል።

እየተሰራ ያለውን መንገድ ደህንነት በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም