ቀጥታ፡

ዓባይን መቀነቷ ጣናን ትራሷ አድርጋ የውበት አክሊል የደፋችው ከተማ 

ዓባይን መቀነቷ ጣናን ትራሷ አድርጋ የውበት አክሊል የደፋችው ከተማ... 

በመለሰ ይነሱ (ኢዜአ)

ባህር ዳር ተፈጥሮ አድልታ የሰጠቻት ከተማ ናት። ጣናን ተንተርሳ፣ ዓባይን እንደ መቀነት ታጥቃ የተቆረቆረችው ይህች ከተማ አሁን ላይ ከተፈጥሮ ስጦታዎቿ ባለፈ በሰው ሰራሽ ጥበብ በኮሪደር ልማት የጣና ውበት ተገልጦና ተሰናስሎ ባህር ዳርን ውብና ማራኪ አድርጓታል።


 

ባህር ዳር የፋሲል ግንብ፣ የሰሜን ተራሮችና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ለሚመጡ መንገደኞች መተላለፊያ ማዕከል ብቻ አይደለችም፤ በራሷ ብርቅና ድንቅ መዳረሻ እንጂ። 

ዓባይን መቀነቷ ጣናን ትራሷ አድርጋ የውበት አክሊል የደፋችው ባህር ዳር ፤የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኝዎችን፣ ባለሀብቶችንና እንግዶችን "ኑ! የተፈጥሮና የዘመናዊነት ጸጋዬን ተቋደሱ" በማለት በአክብሮት ትጣራለች።


 

ባህር ዳር የቀድሞ ትዝታዋን በዘመናዊነት አድሳለች። በሰፋፊ መንገዶቿ ላይ በነጻነት በሳይክል የሚከንፉበት፣ ቀኑን በጭስ አባይ ፏፏቴና በታሪካዊ ገዳማት መንፈስን በማደስ ያሳለፈ እንግዳ፤ ምሽቱን ደግሞ በብርሃን በደመቁት የኮሪደር ልማት ጎዳናዎች እየተንሸራሸረ የሚያመሽባት የመዝናኛ ማዕከል ሆናለች።

በዘንባባ ዛፎቿና በሰፋፊ መንገዶቿ የምትታወቅ ውቧ ባህር ዳር፤ የከተማዋ ፈርጥ የሆነው ጣና፣ የጣና ደሴቶች፣ ታሪክ ጠገብ ገዳማቱ እና በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጢስ ዓባይ ፏፏቴ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ የገዙ ናቸው።


 

በድምሩ ባህር ዳር፣ የጣና ገዳማትና ጎርጎራ የሀገር ታሪክ፣ መንፈሳዊነት እና ተፈጥሮ በልዩ ሁኔታ የተሳሰሩባቸው ድንቅ ቦታዎች ስለመሆናቸው ያዩት ሁሉ የሚመሰክሩት እውነታ ነው።

በመሆኑም እነዚህን እምቅ የመስህብ ሃብቶች በመደመር የልማት አቅምን በመጨመር ለጎብኝዎች፣ ለባለሃብቶችና ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ምቹና ተመራጭ የማድረግ ስራ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።


 

"ለባህር ዳር ተፈጥሮ በራሱ አድልቶላታል" የሚሉት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፤ ሃብትን ገልጦና ውበትን አፍክቶ በመስራት ከተማዋን የጎብኝዎች ማእከል ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የጣናን እና የዓባይ እምቅ ጸጋ ይበልጥ ለማድመቅ የከተማዋን ልማት የሚያፋጥኑ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው የተፈጥሮ ሃብቱን ከከተማዋ መሰረተ ልማት ጋር የማስተሳሰር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። 

በከተማዋ እስካሁን የ6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪው 30 ኪሎ ሜትር ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ይናገራሉ።

የኮሪደር ልማቱ የባህር ዳር የቀድሞ የብስክሌት ትራንስፖርት ባህል እንዲያንሰራራ ማድረግ የቻለ ድንቅ ስራ ሆኗል ብለዋል። 

በተለይም በምሽት በባህር ዳር ከተማ ጎዳናዎች ለመንሸራሸር በውብ መብራቶች ታጅቦ፤ የጣናን ነፋሻማ አየር እየሳቡ መንፈስን በሃሴት መሙላት ይቻላል። 


 

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር በር መክፈቱንና እንደ "መሶብ" ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችም የከተማዋን የንግድና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ማነቃቃቱን ምክትል ከንቲባው ይናገራሉ።

የባህር ዳር አስጎብኚዎች ማህበራትና የጀልባ አገልግሎት ሰጪዎችም የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከተፈጥሮ እሴቷ ላይ ውበት፣ ጽዳትና ምቾት በመጨመር የቱሪዝም  ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርጓል ይላሉ።

በተለይም በውሃ ላይ የትራንስፓርት አገልግሎት የጣናነሽ እና ሌሎች ዘመናዊ ጀልባዎች አገልግሎት ከባህር ዳር ወደ ጎርጎራ ሪዞርት፣ ገዳማቱና ሌሎችም የመስህብ ስፍራዎች ለመድረስ ጉዞውን ቀላል አድርጎታል። 

ባህር ዳር መተላለፊያ ብቻ አይደለችም፤ መቆያ እንጂ! በዘመናዊ ሆቴሎቿ፣ በጽዱ ጎዳናዎቿና በእንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎቿ እንግዶቿን በፍቅር ትቀበላለች። ተፈጥሮ ያደላላት፣ የሰው ልጅ ጥበብ ያደመቃት ባህር ዳር... 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም