በገጠር አካባቢ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ አርሶአደሩን ተጠቃሚ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር አካባቢ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ አርሶአደሩን ተጠቃሚ አድርጓል
ሐረርጌ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት የገጠሩን ማኅበረሰብ ጥያቄ ለመፍታት እያደረገ ባለው ጥረት የተሻለ ኑሮ እንድንመራ አስችሎናል ሲሉ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቡርቃ ዲንቱ ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ።
በወረዳው የሀሮ ጉራቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጀማል አሕመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው በተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የ24 ሠዓት መብራት እያገኙ ነው።
የመብራትና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኝታቸው ኑሯቸውን ቀላል ማድረጉን አንስተዋል።
አርሶ አደር አልቃድር ሼህ አሕመድም መንግሥት የገጠሩን ሕብረተሰብ ኑሮ ለመቀየር በመሥራቱ የተሻለ ኑሮ እንድንመራ እያደረገን ነው ብለዋል።
የቡርቃ ዲንቱ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አሽም ቡሽራ እንዳሉት፤ በፌዴራል መንግሥት የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት የ24 ሠዓት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ አስችሏል።
እስካሁንም በሁለት ቀበሌዎች የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አገልግሎቱን ያገኙ ሲሆን፤ በቀጣይ አራት ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ዳይሬክተር ጥላሁን ብርሃኑ (ኢ/ር)፤ ከዋናው መስመር ርቀው የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቡርቃ ዲንቱ ወረዳ የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫም ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና ከ230 ኪሎ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት የሚችል መሆኑን አመልክተዋል።