ቀጥታ፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጡ ነው

ጎንደር ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጡ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።  

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ግብርናውን ማዘመን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።


 

ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የአየር ንብረትና ስነ-ምህዳር በመጠቀም በመኸር፣ በበጋ መስኖ፣ በከተማ ግብርና እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፋ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ዘላቂ ምርታማነትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች አርሶ አደሩ ከፍጆታ ያለፈ ትርፍ ምርት እንዲያመርት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ለማምረት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ በመኸርና በመስኖ ሰብል ልማት፣ በደንና ሌሎች የልማት ስራዎች ለወጣቶች አዳዲስ የስራ እድሎች ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት በማረጋገጥም ሀገራችን በምግብ ራስን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት ለማሳካት የግብርና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ላይ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አዳነ መሀሪ (ዶ/ር) በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በመሬት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ 600 በላይ ባለሀብቶች ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በገበያ ተኮር ምርቶች በተለይም በሰሊጥ፣ በጥጥና በአኩሪ አተር ልማት ላይ ተሰማርተው ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።


 

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ጣቢያዎቹ አማካኝነት የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ፣ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በፎረሙ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና አጋር አካላት እየተሳተፉ ሲሆን፣ በቀጣይም የግብርና ኢንቨስትመንቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም