ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለግል ዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ኢኮኖሚው እየተነቃቃ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለግል ዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ኢኮኖሚው እየተነቃቃ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ግሎባል ኮምፓክት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንዳ ኦጃምቦ ገለጹ።


 

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለኢኮኖሚው ማደግ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝትም እጅግ ከፍተኛ የሆነ ልማት እና ለውጥ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ በተሠሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ተግባራት ምክንያት፤ ሪል ስቴት፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎች ዘርፎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

የባንክ እና የቴሌ-ኮሙኒኬሽን ዘርፎችን ለገበያ ክፍት የማድረግ (ሊበራላይዜሽን) እርምጃዎችም የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻሉን አመላክተዋል።

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ፋይዳም አንስተዋል።

በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ኢኮኖሚዎች አብዛኞቹ በአፍሪካ የሚገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።


 

ይህም አፍሪካን ለኢንቨስትመንት አስቸጋሪ አድርጎ የመመልከት የተሳሳተ አመለካከትን በመቀየር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።

አሁን አፍሪካ ከጥገኝነት ወጥታ በራሷ ዐቅም ላይ የምትደገፍና ለራሷ ኢንቨስትመንት ቅድሚያ የምትሰጥበት ጊዜ ላይ መሆኗንም አስገንዝበዋል።


 

አፍሪካውያን በአኅጉራቸው ላይ በስፋት መሰማራት እንዲችሉ የሀገር ውስጥ ካፒታልን በውጤታማነት ማሰባሰብ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች https://linktr.ee/ENADigital

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም