የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲሱ ገጽታ፤ ከአማራጭ ማጣት ወደ መዳረሻዎች ብዛት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲሱ ገጽታ፤ ከአማራጭ ማጣት ወደ መዳረሻዎች ብዛት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በታሪክና በተፈጥሮ የታደለች ምድር ብትሆንም ለዘመናት የዘርፉ ዋነኛ ፈተና የመዳረሻዎች ውስንነት ነበር።
ጎብኚዎች ጥቂት የታወቁ ቦታዎችን ተመልክተው ቶሎ የሚመለሱባት ሀገር ነበረች፤ አሁን ላይ ግን ያ የቆየ ታሪክ በፈጠራና በቁርጠኝነት እየተቀየረ ነው።
ሀገሪቱ ከአማራጭ ማጣት ወጥታ የመዳረሻዎች ብዛትና ጥራት ወደተሰናሰሉበት አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት እና የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገንባት ስልታዊ ዐቅም አለው።
ቱሪዝም ሲያድግ ብቻውን አይደለም፤ ግብርናን ያነቃቃል፣ ትራንስፖርትና ግንባታን ያፋጥናል እንዲሁም የባህል አልባሳትና ቅርጻ ቅርጾችን የሚያመርቱ አነስተኛ ተቋማትን ኢኮኖሚ ያሳድጋል።
ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመሩት ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የቱሪዝም ካርታ ከመሠረቱ ቀይረውታል።
ለአብነትም በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ የተገነቡ ዘመናዊ መዳረሻዎች ተፈጥሮን ከታሪክ፣ ምቾትን ከዘመናዊነት ጋር አሳምረው የያዙ የኢትዮጵያ አዲስ የቱሪዝም ጌጦች ሆነዋል።
እነዚህ ሥራዎችም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማደግን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ሀገር እንዲያደርጓት ትልቅ ምክንያት ሆነዋል፡፡
የሰለብሪቲ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አሸናፊ ካሳ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የነበረው የመዳረሻዎች እጥረት አሁን ላይ ተቀርፏል።
ቱሪስቶች ከጥቂት ታሪካዊ ቦታዎች ወጥተው ብዙ የሚቆዩባቸው አማራጮች ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
የፕሌዥር ኢትዮጵያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ሥራ አስኪያጅ ናሆም አድማሱ በበኩላቸው ቀደም ሲል ውብ ቦታዎች ቢኖሩም የሚመጥን ማረፊያ ባለመኖሩ ይታለፉ እንደነበር አውስተዋል።
አሁን ግን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጂዎችና ሪዞርቶች በመገንባታቸው ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ምክንያት ሆኗቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የመዳረሻዎቹ መብዛት ለአስጎብኚዎችም አዲስ የፈጠራ በር መክፈቱን የገለጹት ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አሸናፊ ካሳ፤ ናይት አውት የተሰኘው አዲስ የጉብኝት ፓኬጅ እንግዶች በምሽት የከተማዋን ውበት እንዲያጣጥሙ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ይህም ተጨማሪ ገቢን ለማግኘት፣ የሥራ ዕድልና ረዘም ያለ የቱሪስት ቆይታ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የጀመረችው ጉዞ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያመጣ እንደሚገኝ ነው አስተያየት ሰጭዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
መንግሥት የጀመረው መዳረሻዎችን የማስፋፋት ሥራ ሀገሪቱን በዓለም የቱሪዝም መድረክ ተወዳዳሪ ከማድረጉም ባለፈ፤ ለጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ትልቅ የጀርባ አጥንት እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ የታሪክ ብቻ ሳትሆን የዘመናዊ መዳረሻዎችም መፍለቂያ መሆኗንም አመላክተዋል።